አብሮነት መጪው ምርጫ እንዲራዘምና የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጠየቀ
አብሮነት መጪው ሃገራዊ ምርጫ እንዲራዘምና የእርቅና የሽግግር መንግስት እዲቋቋም ጠየቀ
ምርጫ ቦርድ መጪው ሃገራዊ ምርጫ ነሃሴ 10 ቀን 2012 ዓ/ም ይካሄዳል በሚል በጊዜያዊነት ያስቀመጠውን የምርጫ ሰሌዳ በተመለከተ ሰፊ ግምገማ ማድረጉን ያስታወቀው አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) ምርጫው እንዲራዘምና የእርቅና የሽግግር መንግስት እዲቋቋም ጠይቋል፡፡
ጥምረቱ ወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ መግለጫን ሰጥቷል፡፡ በመግለጫው ኢትዮጵያ በብሄራዊ የደህንነት ስጋት ውስጥ እንደምትገኝ ነው ያስታወቀው፡፡ የተጀመረው ሃገራዊ ለውጥ ውጤታማነት ሳይረጋገጥ፣ህዝብ እንደልቡ መንቀሳቀስ በማይችልበትና የጸጥታና ደህንት ስጋቶች ባልተቀረፉበት መንግስትም ህግና ስርዓትን ማስከበር ባልቻለበት ሁኔታ ምርጫን ማካሄዱ የከፋ ጉዳት አለው ብሏል፡፡
በአሁኑ ውቀት ከምርጫ ይልቅ ለሃገር ማሰብ ይቀድማል ያለም ሲሆን ምርጫው ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘምና የእርቅና የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጠይቋል፡፡
ሃገርና ህዝብ ችግር ላይ ሆነው ሳለ መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ምርጫ ይካሄድ ማለታቸው ተገቢ እንዳይደለና ከፍተኛ ሃገራዊ ተጠያቂነት እንዳለባቸውም ነው ያስታወቀው፡፡በምርጫ ወቅትም ሆነ ከምርጫ በኃላ ለሚፈጠሩ ችግሮች፣ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ጉዳቶችም ኃላፊነትን ይወስዳሉም ነው ያለው፡፡
በጸደቀው የምርጫ አዋጅ ላይ ስምምነት ላይ ባልተደረሰበት ሁኔታ ምርጫ ቦርድ ዝርዝር የምርጫ አፈጻጸም ረቂቅ ደንቦችን ማውጣቱን ተገቢነት የለውም በሚልም ኮንኗል፡፡ዝርዝር የምርጫ የጊዜ ሰሌዳው ባልጸደቀበት ሁኔታ ብልጽግናን እና ኦፌኮን መሰል አንዳንድ ፓርቲዎች ቅስቀሳን በግልጽ መጀመራቸው የሚያስጠይቅ ነውም ነው ያለው፡፡
አብሮነት የምርጫ ቁሳቁሶች በውጭ ሃገራት ይታተማሉ መባሉንም ተቃውሟል፡፡ የውጭ ኃይሎችን ለጣልቃ ገብነት የሚጋብዝ እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡ አደጉ የሚባሉ ሃገራት እንኳን ሳይቀሩ በሌሎች አካላት ያልቃ ገብነት በሚቸገሩበት በዚህ ወቅት የምርጫ ቁሳቁሶች በማናውቀው ኃይል መታተም የለባቸውም ያለም ሲሆን ነገሮች በጋራ ሊወሰኑ እንደሚገባም በመግለጫው አስቀምጧል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባን ዘመናዊ እና ተአማኒ ያደርጋል በሚል የተለያዩ የህትመት ስራዎች ስምምነትን በዱባይ መፈራረሙ የሚታወስ ነው፡፡
አብሮነት ከሁለት ወራት በፊት ታገቱ የተባሉትን የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጉዳይ እጅግ ያስጨነቀና ያሳሰበ በሚል ኮንኗል፡፡ ጉዳዩ ህብረተሰቡን ቢያስጨንቅና አደባባይ እስከመውጣት ቢያደርስም መንግስት ያሳሰበው አይመስል፤ግልጽ መረጃን እየሰጠም አይደለም ሲልም ነው የወቀሰው፡፡
ታጋቾቹ ያሉበት ሁኔታ በውል አለመታወቁን ተከትሎ ህዝብ ለከፍተኛ ግራ መጋባትና ጭንቀት በመዳረጉ መንግስት ከየትኛውም ጉዳይ በላይ ለተማሪዎቹ ትኩረት በመስጠት እንዲሰራ እና ያሉበትን ሁኔታ በግልጽ በአስቸኳይ እንዲያሳውቅ ጠይቋል፡፡
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ በኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን) እና በኅብር ኢትዮጵያ ጥምረት የተመሰረተ ነው፡፡