ሩሲያ ከሶስት ዓመት በላይ በአገሯ የቆዩ አሜሪካዊያን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች
ሩሲያ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው አሜሪካ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰዷ ነው
ሶስት ዓመት እና ከዚያ በላይ አሜሪካዊያን እስከ መጭው ጥር ድረስ እንዲለቁ ሩሲያ አሳስባለች
ሩሲያ ከሶስት ዓመት በላይ በአገሯ የቆዩ አሜሪካዊያን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች፡፡
አሜሪካ ከአንድ ወር በፊት ባስተላለፈችው ውሳኔ ሶስት ዓመት እና ከዚያ በላይ በአሜሪካ የሚኖሩ ዲፕሎማቶች እስከ ቀጣዩ ጥር ወር ድረስ አገሯን ለቀው እንዲወጡ አዛለች፡፡
በዚህ የአሜሪካ ውሳኔ የተበሳጨች የምትመስለው ሩሲያ ተመሳሳይ ውሳኔ ማስተላለፏን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ገልጻለች፡፡
“የኤምባሲ ሰራተኞችን ወይም የቤተሰቦቻቸውን አባላት ከሀገር የማስወጣት እቅድ የለም “- የሩሲያ ኤምባሲ
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ሶስት ዓመት እና ከዚያ በላይ በሩሲያ የሚኖሩ አሜሪካዊ ዲፕሎማቶች እስከ ቀጣዩ ጥር 2022 ዓመት ድረስ ለቀው እንዲወጡ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ እንዲሆን የፈለገችው አሜሪካ ናት ያሉት ቃል አቀባይዋ ሩሲያም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ትገደዳለች ሲሉ አክለዋል፡፡
አሜሪካ እስከ ቀጣዩ ሀምሌ ወር ድረስም የሶስት ዓመት ህግ በሚል የጀመረችውን አሰራር ካላስቀረች ሩሲያም ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰዷን ትቀጥላለች ሲሉም ቃል አቀባይዋ አስጠንቅቀዋል፡፡
በዋሸንግተን የሩሲያ አምባሳደር አንቶሊ አንቶኖቭ እንዳሉት በአሜሪካ የተለያ ግዛቶች ያሉ 27 የሩሲያ ዲፕሎማቶች እና ቤተሰቦቻቸው እስከ መጭው ጥር ወር ድረስ ተገደው አሜሪካን ይለቃሉ ብለዋል፡፡
የነጩ ቤተመንግስት ምክትል ቃል አቀባይ ጃሊና ፖርተር በበኩላቸው እስከ ቀጣዩ ጥር ወር ድረስ 50 የሩሲያ ዲፕሎማቶች አሜሪካን ለቀው እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ይህ የአሜሪካ ውሳኔ ዲፕሎማቶችን ማባረር ነው ተብሎ መጠራት የለበትም ብለዋል፡፡