ኖርዌይ ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና እንደምትሰጥ አስታወቀች
ቴልአቪቭ ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና መስጠት ማለት ሀማስ እንዲፈረጥም መፍቀድ ማለት ነው ትላለች
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስተር ጆናስ ጋርስቶር መንግስታቸው ለፍልሰጤም ሙሉ የሀገርነት እውቅና ለመስጠት መወሰኑን አስታውቀዋል
ጠቅላይ ሚንስተሩ ‘’በጋዛ እየሆነ ያለውን ለማስቆም እስራኤል እና ፍልስጤም ሁለት የተለያዩ ሀገራት መሆናቸውን መቀበል አስፈላጊ ነው፤ ይህን ለማረጋገገጥ ደግሞ ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና መሰጠት ግድ ነው’’ ብለዋል፡፡
በጋዛ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀንን የቀጠፈው ጦርነት ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ሌሎች ሀገራትም የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ ጠይቀዋል፡፡
እውቅናው ከሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ ተግበራዊ የሚደረግ ሲሆን ኖርዌይ ከፍልስጤም ጋር የሚኖራት ግንኙነትን የሚወስኑ ጉዳዮች በቅርቡ ይፋ ይደረጋሉ ተብሏል።
አየርላንድ እና ስፔን በቀጣይ ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና ለመስጠት እየተጠበቁ ሲሆን ሌሎች አውሮፓ ሀገራትም በተመሳሳይ ይህንኑ ያደርጋሉ ነው የተባለው፡፡
ፖርቹጋል፣ ቤልጅየም፣ ስሎቫኒያ እና ማልታ በጉዳዩ ላይ እያጤኑበት መሆኑ ታውቋል፡፡
ከ35ሺህ በላይ ንጹሀንን የቀጠፈው የጋዛ ጦርነት ምእራቡ አለም በፍልስጤም ላይ ያለውን አተያይ እንዲቀይር ያደረገው ይመስላል፡፡
"ቱ ስቴት ሶልዩሽን" በመባል የሚጠራው በዋናነት ለፍልስጤም የሀገርነት እውቀና መሰጠት ላይ በሚያጠነጥነው እና የእስራኤልንም ገለልተኛ ሀገርነት በሚወስነው ምክረ ሀሳብ ላይ የቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደደር ከፍተኛ ተቃውሞ አለው፡፡
ቴልአቪቭ ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅና መስጠት ማለት ሀማስ እንዲፈረጥም መፍቀድ ማለት ነው ትላለች፡፡
የአውሮፓ ለሁለት መከፈል
አውሮፓ በጉዳዩ ላይ ለሁለት ተከፍሏል።ስፔን፣ ፔልጅየም እና ፖርቹጋልን የመሳሰሉ ሀገራት ፍልስጤም በተከለለ ድንበር እራሷን ችላ ሀገር ሆና መቆሟ እስራኤል ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመሳደር እና የዛን ቀጠና ውጥንቅጥ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ ለመቋጨት መፍትሄ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
በአንጻሩ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያን የመሳሰሉ ሀገራት በጉዳዩ ላይ የተለሳለሰ አቋም የሚያንጸባርቁ ገሚሶችም ከእስራኤል ጋር ባላቸው ወዳጅነት ከነአካቴው የፍልስጤምን ሀገር መሆን የማይቀበሉ ናቸው፡፡
የምእራቡን አለም እና የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናን በተለያየ አቋም ልዩነት የከፋፈለው የፍልስጤም ሀገር የመሆን ነገር ከጀርባው ትልቅ ታሪካዊ እና ጂኦፖለቲክሳዊ ዳራ የተሸከመ ነው።