በጋዛ ሆስፒታሎች የተገኙት ጅምላ መቃብሮች ምርመራ እንዲደረግባቸው የፍልስጤም ባለስልጣናት ጠየቁ
የእስራኤል ጦር ግን የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት የጅምላ መቃብር ፈጽሟል የሚለውን የፍልስጤም ባለስልጣናት ውንጀላ አልቀበለውም ብሏል
የፍልስጤም ሲቪል ዲፌንስ ቡድን በጋዛ በሚገኙ ሆስፒታሎች ተፈጽመዋል ያላቸውን የጦር መንጀሎች ተመድ ምርመራ እንዲያካሄድባቸው ጠይቋል
የፍልስጤም ሲቪል ዲፌንስ ቡድን በጋዛ በሚገኙ ሆስፒታሎች ተፈጽመዋል ያላቸውን የጦር መንጀሎች ተመድ ምርመራ እንዲያካሄድባቸው ጠይቋል።
ቡድኑ እንደገለጸው የእስራኤል ወታደሮች ቦታውን ለቀው ከወጡ በኋላ በሆስፒታሎቹ አጥር ግቢ ውስጥ 400 ሰዎች የተቀበሩባቸው ጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል።
በናስር ሜዲካል ኮምፕሌክስ በህክምና ላይ የነበሩ ሰዎች ጭምር ተገድለዋል ብሏል ቡድኑ።
የፍልስጤም ባለስልጣናት፣ የእስራኤል ወታደሮች ከካን ዮኒስ መውጣታቸውን ተከትሎ ባወጡት ሪፖርት በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኘው ግዙፉ የናስር ሆስፒታል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተቀበሩበትን ጅምላ መቃብር አግኝቷል።
ከዚህ በተጨማሪም የእስራል ልዩ ኃይል ውጊያ ባካሄደበት በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኘው የአል ሽፋ ሆስፒታል ውስጥ አስከሬኖች ተገኝተዋል ተብሏል።
የተመድ የሰብአዊ መብት ኃላፊ ቮልከር ቱርክ እንዳሉት በጋዛ አል ሽፋ እና ናስር ሆስፒታል ላይ በደረሰው ውድመት እና በጅመላ መቃብር ሪፖርቶች መደንገጣቸውን ባለፈው ማክሰኞ ነበር የገለጹት።
የእስራኤል ጦር ግን የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት የጅምላ መቃብር ፈጽሟል የሚለውን የፍልስጤም ባለስልጣናት ውንጀላ አልቀበለውም ብሏል።
ጦሩ የእስራኤል ታጋቾችን ሲፈልግ ቀደም ሲል በአል ናስር ሆስፒታል አቅራቢያ የተቀበሩ አስከሬኖችን ማግኘቱን እና መርምሮ ወደ ቦታቸው መመለሱን ገልጿል።
በሆስፒታሉ ውስጥ የእስራኤል ታጋቾች መቆየታቸውን የሚያመላክቱ የደህንነት መረጃዎች በመገኘታቸው በጥንቃቄ እና የሟቾችን ክብር በመጠበቀ መልኩ ምርመራ መደረጉን የገለጸው ጦሩ፣ የእስራኤል ጦር ግድያ ፈጽሞ በጅምላ ቀብራል የሚለውን ክስ አስተባብሏል።
በዘሄግ የሚገኘው አለምአቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የጥቅምት ሰባቱን ጥቃት እና እሱን ተከትሎ የተፈጸሙ ወንጀሎችን እየመረመረ ነው።
የፍርድ ቤቱ ዋና አቃቤ ህግ ካሪም ካን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎች ላይ በንቃት ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።