በቂ እንቅልፍ አለመተኛት የሚያስከትላቸው የጤና ጉዳቶች ምንድን ናቸው?
ከአጠቃላይ የአለም ህዝብ 25 በመቶ የሚሆነው በተለያዩ ምክንያቶች በቂ እንቅልፍ አያገኝም

ካንሰር ፣ የመርሳት በሽታ ፣ ዝቅተኛ የማሰላሰል ብቃት እና ሌሎችንም አዕምሯዊ እና አካላዊ የጤና እክሎችን ሊያስከትል እንደሚችል ሳይንስ አረጋግጧል
የሰው ልጅ በመሰረታዊነት ከሚያስፈልጉት ተፈጥሯዊ ዑደቶች መካከል አንዱ የሆነው እንቅልፍ አዕምሮ እና አካል በቂ ረፍት አግኘቶ በሀይል እንዲሞላ ወሳኝ ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡
እንቅልፍ በሁሉም የሰው ልጅ ሥርዓት ላይ ተጽዕኖ ከማሳደሩም ባለፈ ጥሩ የምሽት እረፍት ማግኘት ለምን ያህል አመት እንደሚኖሩም ጭምር ሊወስን ይችላል፡፡
የአውስትራሊያው ፍሊንደርስ ዩኒቨርሲቲ የእንቅልፍ ህክምና ተመራማሪ ሃና ስኮት እድሜያቸው ከ18 እስከ 65 የሆኑ አዋቂዎች በቀን ከሰባት እስከ ዘጠኝ ሰአታት ከ65 አመት በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከሰባት እስከ ስምንት ሰአት መተኛት እንደሚጠበቅባቸው ይናገራሉ፡፡
ጥናቶች እንደሚያመላክቱት 25 በመቶ የሚሆኑ የአለም ህዝቦች በተለያዩ ምክንቶች በእያንዳንዱ ምሽት በቂ እንቅልፍ አያገኙም።
የእንቅልፍ ጤናማነት የሚለካው በሰአታት እርዝማኔ ብቻ ሳይሆን ከመደበኛነቱ እና በተከታታይ ቀን ከእንቅልፍ በሚነቁበት ሰአትም ጭምር ነው፡፡
የእንቅልፍ ህክምና ተመራማሪዋ ሃና ስኮት እንደሚሉት በቅርብ ጊዜ የተገኙ የጥናት ውጤቶች የሚያሳዩት መደበኛ ባልሆነ የእንቅልፍ ስርአት ምክንያት የሚከሰቱ አዕምሯዊ እና አካላዊ የጤና እክሎች መስፋፋታቸውን ነው፡፡
የእንቅልፍ እጦት በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት የሚችል ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል የእንቅልፍ ሰአት መዛባት፣ የምሽት ፈረቃ ሥራ፣ ልጅ ማሳደግ ፣ ሥር የሰደደ ሕመም፣ የእድሜ መገፋት እና ለረጅም ጊዜ ስልክን አብዝቶ መጠቀም ይጠቀሳሉ፡፡
በምዕራብ አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ የእንቅልፍ ሳይንስ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ጄን ዋልሽ በተለያየ ጊዜ ያመለጠ እንቅልፍ የኋላ ኋላ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
የእንቅልፍ መዛባት ወይም ዕጥረት በአካል እና በአዕምሮ ጤና ላይ ከሚያስከትላቸው የጤና እክሎች መካከል ጥቂቶችን እንመልከት፡፡
የስሜት እና የአዕምሮ ጤና
በአንጎል ውስጥ ያሉ የነርቭ ሴሎች ሲተኙ ጠንካራ አቅም የሚያገኙበትን እረፍት መላበስ ያስችላቸዋል፡፡
ነገር ግን በቂ እና ጥራት ያለው እንቅልፍ ካላገኙ በሚቀጥለው ቀን አዲስ ግንኙነት ለመፍጠር ይቸገራሉ ይህም መረጃን የመገምገም እና የማገናዘብ ችሎታን ይጎዳል።
በዚህ የተነሳ ሰውነትዎ እንደ አድሬናሊን እና ኮርቲሶል ያሉ የጭንቀት ሆርሞኖችን በማመንጨት የብስጭት እና የመነጫነጭ ስሜት እንዲሰማዎት ፣ ለውሳኔ እና ለመደምደም ፈጣን እንዲሆኑ እንዲሁም ትዕግስትን በማሳጣት ቁጡ እንዲሆኑ ሊያደርግ ይችላል
እንቅልፍ ማጣት የወሲብ ፍላጎትዎን እና መነቃቃትን ሊቀንስ ይችላል፤ በሳምንት ውስጥ በቀን ለአምስት ሰአታት ብቻ የሚተኙ ሰዎች የቴስቶስትሮን መጠናቸው እስከ 15 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ምርምሮች ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም የመንፈስ ጭንቀትን፣ ድብርት፣ ለስሜት መለዋወጥ (ባይፖላር ዲስኦርደር) የመጋለጥ ወይም የማባባስ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችልም ተነግሯል፡፡
ስኳር እና የልብ ህመም
አንዳንድ የእንቅልፍ ማጣት ውጤቶች የበለጠ አደገኛ እና ለህይወት ሊያሰጉ እንደሚችሉ ፤ ችግሩ የተባባሰ እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ከሆነም እንደ ቀላል መታየት እንደሌለበት በምዕራብ አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ የእንቅልፍ ሳይንስ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ጄን ዋልሽ ይናገራሉ፡፡
የማያቋርጥ ደካማ እንቅልፍ ሳይቶኪን የሚባሉ የኢንፌክሽን ፕሮቲኖችን በማምረት ረገድ ሚና ሊጫወት ይችላል።
ይህም የመተንፈሻ አካላት በሽታ እና ዕብጠት ፣ አስም እንዲሁም ለደም ቧንቧዎች ውፍረት ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ ከዚህ ባለፈም በደም ውስጥ ያለውን ግልኮስ (ስኳር) የሚቆጣጠረው ኢንሱሊን ስርዐት እንዲዛባ በማድረግ ታይፕ 2 የተሰኘውን የስኳር በሽታ የማስከተል እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
ለልብ ሕመም ወይም ለስኳር በሽታ መፈጠር ብቸኛው ምክንያት እንቅልፍ ባይሆንም ነገር ግን አንድ መጥፎ ሌሊት ያለእንቅልፍ ማሳለፍ የደም ግፊትን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል መዘንጋት የለበትም ተብሏል፡፡
ከፍተኛ የካንሰር ተጋላጭነት
አንዳንድ ጥናቶች ደካማ እንቅልፍ የጡት እና የእጢ ካሰርን ከመሳሰሉ በሽታዎች መፈጠር ጋር ግንኙነት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የሌሊት ፈረቃ ለረጅም ጊዜ መሥራት ከአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች ጋር ሊገናኝ እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃም በቅርብ ጊዜ ምርምር ተገኝቷል።
ይህ ሊከሰት የሚችለው በሌሊት የሚሰሩ ሰዎች ሰውነት ከለመደው የጨለማ እና የብርሀን ኡደት ልማድ ጋር ስለሚጋጭ የችግሩ ተጠቂ በመሆን ቀዳሚዎቹ በመሆናቸው ነው፡፡
ሰውነታችን ከለመደው የእንቅልፍ ሰአት ጋር በሚቆራረጥበት ጊዜ ህመምን የመቻል እና በሽታን የመቋቋም አቅምን ሊያዳክም እንደሚችልም ጥናቱ ገልጿል፡፡
የማስታወስ ችሎታ መቀነስ ፣ ያልተፈለገ ውፍረት ፣ አልዛይመር እና ሌሎችም ከእንቅልፍ እጦት ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎች ናቸው ተብሏል፡፡