የሳቅ መሳቅ የጤና በረከቶች ምን ምን ናቸው?
የዓለም የመሳቅ ቀን በዛሬው ዕለት እየተከበረ ነው
አዋቂዎች በቀን ከ15 ጊዜ ህጻናት ደግሞ ከ400 ጊዜ በላይ እንደሚስቁ ይጠበቃል
የሳቅ ጥቅሞች ምን ምን ናቸው?
የመሳቅ ቀን በየ ዓመቱ በፈረንጆቹ ግንቦት አምስት ቀን በመላው ዓለም ይከበራል።
ለመሆኑ የሳቅ ጥቅሞች ምን ምን ናቸው?
በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሳቅ መሳቅ ለጤና አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ነው።
ለአብነትም ሳቅ መሳቅ ከሚያስገኛቸው የጤና በረከቶች መካከል አንዱ በሽታ የመከላከል አቅማችንን በማሳደግ ይታወቃል።
ሌላኛው የሳቅ ጥቅም ደግሞ በስራችን ውጤታማ እንድንሆን ያደርጋል መባሉ ሲሆን በተለይም በስራ አካባቢ ፈገግታ ማሳየት በሰራተኞች እና ተገልጋዮች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋልም ተብሏል።
እንዲሁም ሳቅ መሳቅ የስራ ተነሳሽነትን በመፍጠር በስራ ላይ ውጤታማነት እንደሚጨምር በጥናቶቹ ላይ ተጠቅሷል።
ሳቅ በምንስቅበት ወቅት በሰውነታችን ውስጥ የደስታ ስሜት እንዲሰማን የሚያደርጉ ሆርሞኖች ይነቃቃሉ የተባለ ሲሆን ይህም ሰውነታችን የሚገጥሙትን የጤና እክሎች በሚገባ ምላሽ እንዲሰጥ ያደርጋሉ ተብሏል።
እንዲሁም አዕምሯችን እንደ ድብርት፣ ጭንቀት እና ውጥረት ስሜቶችን እንዲያስወግድ በተቻለ መጠን መሳቅን ማዘውተር እንደሚገባ እነዚሁ ጥናቶች ያስረዳሉ።
ሳቅ መሳቅ በሚያበረክታቸው የጤና ጥቅሞች ምክንያትም የዓለም ጤና ድርጅት በየ ዓመቱ ግንቦት አምስት ላይ ስለ ሳቅ ጥቅሞች ግንዛቤ በመፍጠር እና ሰዎች በተቻለ መጠን ፈገግታን እንዲለማመዱ በማስተማር ዕለቱ ታስቦ ይውላል።
እንደ ጥናቶች ከሆነ አዋቂ ሰዎች በቀን በአማካኝ 15 ጊዜ እና ከዛ በላይ እንዲሁም ህጻናት ደግሞ በቀን እስከ 400 ጊዜ እና ከዛ በላይ እንደሚስቁ ተገልጿል።