ሩሲያ ኒዩክሌር መታጠቋ ከደህንነት ስጋት ጠብቋታል - ላቭሮቭ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምዕራባውያንን የኒዩክሌር ጦርነት ሊከሰት እንደሚችል ደጋግመን እያስታወስናቸው ነው ብለዋል
ሩሲያ ታክቲካል የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን ወደ ቤላሩስ መላኳ ይታወሳል
ሩሲያ የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ መታጠቋ ከየትኛው የውጭ ሃይል የደህንነት ስጋት እየጠበቃት ነው አሉ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ።
ሚኒስትሩ “ኢንተርናሽናል አፌርስ” ከተሰኘው የሀገሪቱ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ሞስኮ ለምዕራባውያን የኒዩክሌር ጦርነት አደጋን ማስታወሷን ቀጥላለች ብለዋል።
“በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ለተደቀነባት የውጭ ሃይሎች የደህንነት ስጋት ምላሽ መስጠት የምንችለው በኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የሩሲያ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭም ባለፈው ወር ዩክሬን የጀመረችው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ስኬታማ የሚሆን ከሆነ ሩሲያ የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን ልትጠቀም ትችላለች ማለታቸው ይታወሳል።
የኬቭ መልሶ ማጥቃት በተፈለገው ፍጥነት መሄድ ባይችልም ምዕራባውያን የሚያደርጉት የመሳሪያ ድጋፍ ግን ቀጥሏል።
ይህ የመሳሪያ ድጋፍ መቀጠል አሜሪካ እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በመጨረሻም ኒዩክሌር ከታጠቀችው ሩሲያ ጋር በቀጥታ ፍልሚያ ውስጥ እንደሚከታቸው ነው ላቭሮቭ የተናገሩት።
ይህን የኒዩክሌር ጦርነት ለማስቀረትም ሊደርስ የሚችለውን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ ለምዕራባውያኑ ደጋግመን እየነገርናቸው ነው ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ ታክቲካል የኒዩክሌር መሳሪያ እጠቀማለሁ በሚለው ዛቻዋ “የእውነት” ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
የኔቶ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግ ግን በሩሲያ የኒዩክሌር ሃይል ዙሪያ ምንም የተለወጠ ነገር አላየንም ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሩሲያ ታክቲካል የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን ያከማቸችባት ቤላሩስ በበኩሏ የውጭ ወረራ ከተከሰተ የሞስኮን የኒዩክሌር መሳሪያዎች እንደምትተኩስ ዝታለች።
በዋሽንግተን የሚገኘው የአለም የጦርነት ጉዳዮች ጥናት ማዕከል፥ ሩሲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኒዩክሌር ጦርነት ሊከሰት እንደሚችል ደጋግማ ማንሳቷ ዩክሬን በጦርነቱ እንዳትገፋ ለማስጠንቀቅ ነው ይላል።
የኒይክሌር ፍልሚያ ስጋትን የማናር የሞስኮ አካሄድንም “የመረጃ ጦርነት” ሲል ይገልጸዋል።