ጀ ባይደን ፤ “ፕሬዝዳት ፑቲን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ስለመጠቀም ሲናገር እየቀለደ አይደም” አሉ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ የኒውክሌር ስጋት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመልሶ እየመጣ ነው ብለዋል
ፑቲን፤ በዩክሬን ጦርነት አስፈላጊ ሆኖ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመጠቀም እንደሚገደዱ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ “ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የኒውክሌር አርማጌዶን ስጋት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመልሶ እየመጣ ነው” አሉ።
ፕሬዝዳንቱ በኒውዮርክ በተካሄደው የዴሞክራቲክ ፓርቲ የገንዘብ ማሰባሰብያ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “በፈረንጆቹ በ1962 ካጋጠመው የኬኔዲ እና ኩባ ሚሳዔል ቀውስ ጀምሮ የአርማጌዶንን ስጋት ገጥሞን አያውቅም ነበር፤ ነገር ግን አሁን ከፍተኛ ስጋት ተጋርጦብናል” ብለዋል።
የፕሬዝዳንቱ ንግግር የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ያነጣጠረ እንደነበርም ነው የኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ የሚያመላክተው።
ፑቲን የዩክሬንን ዘመቻ ለማጠናከር የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመጠቀም ሲያስፈራሩ “እየቀለዱ አይደለም” ሲሉም ፐሬዝዳንት ባይደን ተናግረዋል።
በሶቪየት ህብረት ሚሳዔሎች ኩባ ላይ ተቀስቅሶ የነበረውን የኒውክሌር ግጭት እንደአብነት ያነሱት ባይደን ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ ከኩባ የሚሳዔል ቀውስ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኒውክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀም ላይ ቀጥተኛ ስጋት አለን" ሲሉ ተደምጠዋል።
ፑቲን፤ የዩክሬን ግዛቶችን ለመቆጣጠር አቅም የሚያነስ ሆኖ ከተሰማቸውና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመጠቀም እንደሚገደዱ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም።
የዘርፉ ባለሙያዎች ከሞስኮ ሊሰነዘሩ የሚችሉ የኒውክሌር ጥቃቶች በአንጻራዊነት አነስተኛና ስልታዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምታቸው ቢያስቀምጡም በሁኔታው ከፍተኛ ስጋት ያደረባቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን ግን የኒውክሌር መዘዝ ቀላል ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል።
ባይደን በተወሰነ ቦታ ላይ የሚደረግ ስልታዊ ጥቃት ሰፋ ያለ ግጭት የመቀስቀስና አደጋን የመፍጠር እድሉ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
"በአግባቡ የማውቀው ሰው አለ" ያሉት ጆ-ባይደን "ፑቲን ስለ ታክቲካል ኒውክሌር ጦር መሳሪያ ወይም ባዮሎጂካል ወይም ኬሚካላዊ የጦር መሳሪያዎች አጠቃቀም ሲናገሩ አይቀልዱም ምክንያቱም ወታደራዊው ኃይላቸው በጣም ዝቅተኛ ነው ማለት ይቻላል" ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ታክቲካል ኒውክሌር ጦር መሳሪያን በቀላሉ (መጠቀም) እና ነገሩን አርማጌዶን ላለማድረግ የሚያስችል አቅም ያለም አይመስለኝምም ብለዋል ባይደን።
ሞስኮ፤ በሩሲያ ኃየሎች ስር የሚገኙትን የዶንባስ ግዛቶችን ለመከላከል ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር ጦር ማሳሪያ ልትጠቀም እንምትችል በቅርቡ ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
ከፑቲን በተጨማሪ የቀድሞ የሩስያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በቅርቡ ሩሲያ የዶንባስ ግዛቶች ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም አደጋ ለመከላከል ፤ አስፈላጊ ነው የሚባለው የትኛውም የጦር መሳሪያ በጥቅም ላይ ታውላለች ማለታቸውም አይዘነጋም።
“ስትራቴጂክ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ጨምሮ ሞስኮ ያላትን የትኛውም የጦር መሳሪያ እንጠቀማለን” ነበር ያሉት ሜድቬዴቭ።