በ2022 የአለም መሪዎች አዝናኝ ገጠመኞችና የአፍ ወለምታዎች ምን ይመስላሉ?
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በ2022 በሚያስቁም ሆነ ትዝብትን በሚያጭሩ አጋጣሚዎች የሚደርስባቸው የለም
የብሪታንያው ንጉስ ቻርለስ ሶስተኛ፣ የካናዳ፣ ብሪታንያ እና ፊንላንድ መሪዎችም በ2022 የፈጸሙትን የተለየና ድንገቴ ነገር የካሜራ ባለሙያዎች አስቀርተዋቸዋል
ሊጠናቀቅ የቀናት እድሜ የቀረው የፈረንጆቹ 2022 የአለም መሪዎች ፈገግ የሚያሰኙ ምስሎች በስፋት የተዘዋወሩበት ነበር።
ምን ነክቷቸው ነው ያስባሉ ድርጊቶችን ሲፈጸሙና ንግግር ሲያደርጉ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም ተጋርተው በርካቶች ተመልክተዋቸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም መነጋገሪያ ከሆኑት መሪዎች የአምበሳውን ደርሻ ይወስዳሉ።
የ80 አመቱ አዛውንት በጥር ወር 2022 የፎክስ ኒውስን ጋዜጠኛ መግለጫ እየሰጡ እያለ የተሳደቡበት ገጠመኝ የ2022 አሳፋሪው ጅማሯቸው ነው።
ፕሬዚዳንቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከሰጡ በኋላ “ደደብ የውሻ ልጅ” ብለው መሳደባቸው የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽ ነገር ሆኖባቸዋል።
በመጋቢት ወር 2022ትም ባይደን ከፕሬዚዳንታዊ አውሮፕላን ለመውረድ ሲሞክሩ ሶስት ጊዜ መውደቃቸው የፈገግታ ምንጭ መሆኑ አይዘነጋም።
በሰኔ ወርም ፕሬዚዳንት ባይደን በድጋሚ አውሮፕላን ላይ መውጣት ሲሳናቸው የሚያሳይ ምስል ተለቆ ነበር።
ከባይደን አስገራሚ የ2022 ገጠመኝ አንዱ በሰሜን ካሮሊና በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ንግግር አድርገው ካጠናቀቁ በኋላ ለሰላምታ እጃቸውን መዘርጋታቸው ነው፥ ከአጠገባቸው ግን ሰው አልነበረም።
ፕሬዚዳንቱ እድሜያቸው እየገፋ መሄዱን የሚያሳብቁ ንግግሮችም በዚሁ የፈረንጆቹ አመት አድርገዋል።
በአንድ አጋጣሚ ራሳቸውን ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስን ደግሞ ቀዳማዊ እመቤት አድርገው የጠቀሱት ባይደን፥ ስለዩክሬኑ ቀውስ ሲያወሩም “የዩክሬን ህዝብና ከአጋራቸው ኢራን ” ብለው ሊቅጥሉ ሲሉ ካማላ ሃሪስ አርማቸዋለች (ሩስያ እና ኢራን)።
ፕሬዚዳንቱ ንግግር የሚያደርጉበት ስክሪን ላይ ንግግራቸውን የሚገሩ ነጥቦችንም (End of quote... repeat the line...) አጃምለው በማንበብም አጃኢብ አስብለዋል።
የብሪታንያው አዲሱ ንጉስ ቻርለስ ሶስተኛም በ2022 ያልተጠበቁ ገጠመኞችን አስተናግደዋል።
ንጉስ ቻርለስ ሶስተኛ በዌልስ መዲና ካርዲፍ የንግስናቸውን ስነስርአት ለመታደም የመጡ በርካታ ሰዎችን የመጨበጣቸው ጉዳይ መነጋገሪያ ነበር። በዚሁ ስነስርአት አንድ ወጣት “ያልተገባ” ጥያቄ አንስቶላቸው በሰላምታ የዛለ ሰውነታቸው መንቀጥቀጥ በመጀመሩ ወዲያውኑ በአጃቢዎቻቸው ገሸሽ ተደርገዋል።
ንጉሱ በሰሜን እንግሊዝ ጉብኝት ሲያደርጉም ከአንዴም ሁለት ጊዜ እንቁላል ተወርውሮባቸዋል።
በካናዳም ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶው ለንደን በንግስት ኤልሳቤት የቀብር ስነስርአት ሊታደሙ መጥተው ከቀብሩ አንድ ስአት በፊት በፒያኖ ታግዘው ሲዘፍኑ የሚያሳይ ቪዲዮ መልቀቃቸው በተለይ ከእንግሊዛውያን ሲያስወቅሳቸው ነበር።
በፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በጥፊ መምታት ስታፌዝ የነበረችው የጣሊያን አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒም ሆነች የፊንላንዷ አቻቸው ሳና ማሪን ዘንድሮ ፈገግ ከሚያሰኙና ከሚያሳፍሩ ገጠመኞች አላመለጡም።
ሳና ማሪን ስትደንስ የሚያሳየው ምስል የፊንላንድ ፖለቲከኞችን ብቻ ሳይሆን ባህር ተሻግሮ በርካቶችን አነታርኳል።
ብሪታንያን ለ44 ቀናት የመራችው ሊዝ ትረስም አጭር የስልጣን ዘመኗ ትዝብት ላይ ከሚጥል ጉዳይ አልታደጋትም።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ በለንደን መኸል በሚገኝ ቅንጡ ሆቴል ከጓደኛዋ ጋር ምሳ ከተመገቡ በኋላ ሂሳብ ለመክፈል የሰጡት ካርድ የማይሰራ ነበር፤ ጓደኛቸው ባይከፍሉ ሊዝ ትረስ ምን ይሆኑ ነበር?
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝም በነሃሴ ወር 2022 ላልጠበቁት ጥያቄ የሰጡት ምላሽ አስገራሚ ነበር።
ለሹልዝ የቀረበው ጥያቄው በሳምንት ስንት ጊዜ ሰውነትዎን ይታጠባሉ (ሻወር ይወስዳሉ) የሚል ነው። ለድንገተኛው ጥያቄ የሳቸው ምላሽም ሰባት ጊዜ የሚል ሆኗል። መራሄ መንግስቱ ጀርመናውያንን የውሃ ፍጆታቸውን እንዲቀንሱ እየወተወቱ በየቀኑ ሰውነቴን እታጠባለሁ ማለታቸውም በትዝብት ብዙዎችን አስቋል።
መሪዎች በ2022 በርካታ ፈገግ የሚያሳኙ ትዝብት ውስጥ የጣሏቸውና አስደንጋጭ ክስተቶችን አስተናግደው በካሜራ ባለሙያዎች ተቀድተው ተመልክተናቸዋል።