የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ የኬንያ የምርጫ ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ አሳሰቡ
ጆሴፕ ቦሬል፤ የፖለቲካና የህብረተሰብ መሪዎች ከማንኛውም አይነት ሁከትና ብጥብጥ መቆጠብ አለባቸው ብለዋል
የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ዊሊያም ሩቶ ማሸነፋቸው ይፋ ቢያደርግም ራይላ የምርጫውን ውጤቱን ውድቅ አድረገውታል
የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል የኬንያ ባለስልጣናት የኬንያ የምርጫን ተከትሎ የተፈጠረው ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሲሉ አሳሰቡ።
ኬንያውያን ነሃሴ 9 ቀን 2022 ላካሄዱት "የተረጋጋ እና ሰላማዊ" ምርጫ የአውሮፓ ህብረት ያደንቃል ያሉት ጆሴፕ ቦሬል፤ ነገር ግን ከምርጫ በኋላ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ ይገባል ብለዋል።
ጆሴፕ ቦሬል "የአውሮፓ ህብረት የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ዊልያም ሩቶ በምርጫው አሸናፊ መሆናቸውን ይፋ ማድረጉን እና ውጤቱን ያልተቀበሉት ራይላ ኦዲንጋ ይግባኝ ማለታቸው ይረዳል፤ ነገር ግን ያሉት አለመግባባቶችና በዚህ ምርጫ ላይ የሚነሱ ስጋቶች በሀገሪቱ ባሉ ህጋዊ መንገዶች በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለባቸው" ሲሉም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
እንደ ኬቢሲ ዘገባ ፤ የፖለቲካ እና የህብረተሰብ መሪዎች ከማንኛውም አይነት ሁከትና ብጥብጥ መቆጠብ አለባቸውም ነው ያሉት ቦሬል።
በሰኔ 2021 የተጀመረው የአውሮፓ ህብረት-ኬንያ ስትራቴጂካዊ ውይይት ከአዲሱ የኬንያ አመራር ጋር የበለጠ እንደሚዳብርም ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ በኬንያ ምርጫ ማግስት የተፈጠረውን ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ስትል በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ተዋናዮችን ተማጽናለቸው።
ሁሉም ወገኖች በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የሚነሱትን ውዝግቦችና ስጋቶች አሁን ባለው የግጭት አፈታት ዘዴዎች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደተባበሩም ጠይቃለች አሜሪካ።
የኬንያ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን 5ኛውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዊሊያም ሩቶ መሆናቸውን ይፋ ቢያደርግም፤ በምርጫው ዋነኛ ተቀናቃኝ የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ውጤቱን እንደማይቀበሉ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ራይላ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ የኮሚሽኑ ዋና ሰብሰባዊ ዋፉላ ቼቡካቲ ይፋ ያደረጉትን የምርጫውን ውጤት ውድቅ ለማስደረግ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያቀኑ ገልጸዋል።
ዋና ሰብሰቢ ዋፉላ ቼቡካቲን "አምባገነን” ብለው በመጥራት አጥብቀው የተቹት ራይላ፤ “ ቼቡካቲ ይፋ ያደረጉትን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ አንቀበለውም” ሲሉም ተደምጠዋል።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ጨምረው በገለልተኛ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች መካከል ልዩነት እያለ ዋፉላ ቼቡካቲ የምርጫ ውጤቱን ይፋ ማድረጋቸው ስህተት እንደሆነም ተናግረዋል።