
ኦነግ፤ ከዚህ በኋላ ኦፌኮ አርማውን እንዳይጠቀም ከልክሏል
የአሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) በአርማ አጠቃቀም ዙሪያ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ደብዳቤ እንደተጻፈለት ለአል ዐይን አማርኛ አረጋገጠ፡፡
የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጊዲና (ፕ/ር) ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አርማን በተመለከተ ኦነግ ስጋት እንዳለው መግለጹን ተናግረዋል፡፡ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር ጃዋር መሐመድ በውጭ ሀገር ከደጋፊዎቻቸውና ከአባሎቻቸው ጋር ባደረጉት ስብሰባ የኦነግን አርማ “ተጠቅመዋል” የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ለኦፌኮ መላኩን ነው ፕ/ር መረራ የገለጹት፡፡
ኦነግ በምርጫ ቦርድ የተመዘገበውን አርማውን የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጃዋር መሐመድ በተደጋጋሚ በመድረኮች ላይ እተጠቀመበት እንደሆነ ገልጿል፡፡ ይሁንና ይህንን ድርጊት በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ባለው አብሮነትና በሀገሪቱ ሕግ መሰረት ኦፌኮ ያስቆማል የሚል እምነት እንደነበረው ኦነግ ገልጿል፡፡
ግንባሩ፤ የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አርማውን የመጠቀማቸው ሁኔታ በመቀጠሉ ደብዳቤ ለመጻፍ መገደዱን አስታውቋል፡፡ ፕ/ር መረራ ይህ ደብዳቤ ቢሯቸው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ ምክትል ሊቀመንበር ጃዋር መሐመድ የኦነግን አርማ እንዳይጠቀሙ እንዲያደርጉላቸው አቶ ዳውድ ኢብሳ ጠይቀዋል፡፡
በዚህም መሰረት ከላይ የተገለጸውን ይዘት የያዘውና በአቶ ዳውድ ኢብሳ የተፈረመው የኦነግ ደብዳቤ በፕሮፌሰር መረራ ዲና ለሚመራው ኦፌኮ መድረሱን ፕ/ር መረራ ገልጸዋል፡፡ ፕ/ር መረራ፤ ደብዳቤው መድረሱን ከገለጹ በኋላ “ይህ የፖለቲካ ልዩነትን አያመለክትም” ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ ሊቀመንበሩ ምላሹ ዝም ማለት አሊያም መልስ መስጠት ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡