ብሔራዊ ምክክሩ በአፍሪካ ህብረት፣ በኢጋድ እና በተመድ የሚመራ ነው
ሱዳንን ከገጠማት ፖለቲካዊ ቀውስስ እንደሚያወጣ ተስፋ የተጣለበት ብሔራዊ ምክክር ዛሬ በካርቱም ተጀመረ፡፡
ምክክሩ በሌ/ጄ አል ቡርሃን የሚመራውን ወታደራዊ መንግስት ጨምሮ ሌሎችን ተቀናቃኝ አካላት የሚያሳትፍ ሲሆን ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት ወደ ምርጫ ለማምራት እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡
የምክክሩን መጀመር አስመልክተው ትናንት ማታ (ማክሰኞ) ለሱዳናውያን መልዕክትን ያስተላለፉት የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የሱዳናውያንን ህልም እውን ለማድረግ ከሁሉም አካላት ጋር በመተባበር እንሰራለን ብለዋል፡፡
ሱዳን ሽግግር ላይ መሆኗን ተከትሎ ስምምነት በመታጣቱ ብዙ ችግሮች ማጋጠማቸውን ያስታወሱት ቡርሃን የሚመሩት ጦር ሽግግሩ እንዲያበቃ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንና ለዚህም ከ2019 ጀምሮ (እ.ኤ.አ) ቃል ገብቶ እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ጦሩ ለምክክሩ የቀረበውን ጥሪ በመቀበል ለስኬታማነቱ እንደሚታገም ነው አዛዡ የተናገሩት፡፡
"በሱዳን የተወሰደው ግዛታችን በየትኛውም መመዘኛ ይመለሳል" - አቶ ደመቀ መኮንን
ቡርሃን ጦሩ በምክክሩ ስምምነት ላይ ለሚደረስባቸው ሃሳቦች ተግራዊነት እንደሚተጋ በመግለጽም ከምርጫ በኋላ ስልጣን እንደሚያስረክብ እና ራሱን ከፖለቲካዊ ተሳትፎ እንደሚያርቅ ቃል ገብተዋል፡፡
"ታሪካዊ" ላሉት ለብሔራዊ ምክክሩ ስኬት ሁሉም ሱዳናውያን የበኩላቸውን እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ብሔራዊ ምክክሩ በአፍሪካ ህብረት፣ በኢጋድ እና በተመድ የሚመራ ነው፡፡
ተመድን ጨምሮ አሜሪካን መሰል ሃገራት ለብሔራዊ ምክክሩ መጀመር ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል፡፡
በቡርሃን የሚመራው ጦር የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ከስልጣን ካስወገደ በኋላ ጥሎት የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በቅርቡ ማንሳቱና እስረኞችን መፍታቱ ይታወሳል፡፡