“ከመድረክ የወጣነው ኦፌኮ ከመድረክ ሕግ ውጭ እየሠራ ስለሆነ ነው” ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ
ከምርጫው ጋር በተያያዘ “ከ 1997 ምርጫ በኋላ ያየነው ሁኔታ እንዲደገም የሚፈልጉ ወገኖች ካሉ እዛ ላይ ስጋት ይኖረኛል” ብለዋል
የኢሶዴፓ ደጋፊዎች ፓርቲው ከመድረክ አባልነት እንዲወጣ መጠየቃቸውን ፕ/ር በየነ ገልጸዋል
ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በተደረጉ ምርጫዎች ላይ የተሳተፉት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ብዙ ፓርቲዎችን አቅፎ የነበረው የመድረክ መሪ ነበሩ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጅ ምሁሩ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ስማቸው ከሚነሳ ፖለቲከኞች መካከል የመጀመሪው ረድፍ ላይ እንደሚቀመጡም ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ ‘የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ’ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በምርጫ 2013 ፣ ከመድረክ ጋር ስላላቸው እሰጥ አገባ ፣ ስለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ እንቅስቃሴ እና ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ም/ ዋና ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ያሉት ፕ/ር በየነ የመንግስት ኃላፊ መሆንና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ መሆን እንደማይጋጭባቸው ይገልጻሉ፡፡ “እኔ አሁን ያለሁበት የሥራ ቦታ ልክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተቀጥሬ እንደምሰራው ነው፤ ከፖለቲካ ጋር በምንም አይጋጭም“ የሚሉት ፕ/ር በየነ “ሀገርን እንድናገለግል ዕድል ሲፈጠር ገብቶ መሥራት መልመድ አለብን“ ብለዋል፡፡
ኢሶዴፓና መድረክ
‘የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ’ የመድረክ አባል የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ከጥምረቱ ስለመውጣቱ ሊቀመንበሩ ለአል ዐይን አረጋግጠዋል፡፡ ኢሶዴፓ ከመድረክ አባልነቱ ራሱን ያገለለበት ምክንያት ኦፌኮ ከመድረክ ሕግ ውጭ እየሰራ በመሆኑ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ምርጫ መካሄድ አለመቻሉን ተከትሎ “ኢሶዴፓ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ እንዳትገባ ሕገ መንግስት ይተርጎም የሚለውን ሲቀበል ኦፌኮ ይህንን አለመቀበሉም” ሌላው ልዩነታቸው መሆኑን ሊቀመንበሩ ፕ/ር በየነ አንስተዋል፡፡
“ሀገራችን ላይ መፍረክረክ እንዳይፈጠር ሕገ መንግስት ይተርጎም የሚለውን ተቀበልን፤ ከዚያ ከተተረጎመም በኋላ ለአንድ ዓመት ምርጫ ይራዘም የሚለውን ኢሶዴፓ ተቀበለ፤ ኦፌኮ ይህንን መቀበል አልፈለገም ነበር“ ያሉት ሊቀመንበሩ “ኦፌኮ እኛ የማናምንባቸውን መግለጫዎች ከማናውቃቸው ድርጅቶች ጋር ማለትም ከኦነግ፣ ከኦብነግ ፣ከአገው ሸንጎና ሌሎችም ጋር ሰጠ፡፡ እኛ ደግሞ ከነዛ ጋር የፈጠርነው ግንኑኘት የለንም” ብለዋል ፡፡
ኢሶዴፓ ከመድረክ የወጣው ፤ ኦፌኮ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በማበሩ ብቻ እንዳልሆነ የሚያነሱት ፕ/ር በየነ ፣ “የሚሰጡት መግለጫም ኃላፊነትን የተላበሰ ነው ብለን መውሰድ ባለመቻላችን ነው” ብለዋል፡፡ ፕ/ር በየነ ከአል ዐይን ጋር ባደረጉት ቆይታ “የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ በጣም አጨቃጫቂ ፣ አከራካሪ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስጋት ውስጥ የሚከት ፕሮፖጋንዳ ውስጥና ህዝብን ማነሳሳት ውስጥ የሚገቡ ሰዎችን በአባልነት ተቀብሏል” ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ አጨቃጫቂና አከራካሪ በሚል የገለጿቸው የኦፌኮ አባላት እነማን እንደሆኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ከምናገረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊረዳው ይችላል ፣ የሰው ስም እያነሱ መናገርን ተገቢ ሆኖ አላየውም” ሲሉ መልሰዋል፡፡
ኢሶዴፓ የመስራች አባላትን ፊርማ በአዲስ አበባ ሲያሰባስብ ከፍተኛ ትችት እንደተሰነዘረባቸው የገለጹት ሊቀመንበሩ “ለኢትዮጵያ ስጋት የሆኑ ድርጅቶች ጋር መድረክ ውስጥ አብራችሁ እስከሰራችሁ ድረስ ‘አጠገባችን አትድረሱ’ ተብለናል” ብለዋል፡፡
“ደጋፊዎቻችን ‘ከመድረክ ራሳችሁን ለዩ፤ ካለበለዚያ የእኛን ድጋፍ አታገኙም’ አሉን፤ ደጋፊ የሌለው ፓርቲ ይዘን ምንድነው የምንሰራው” የሚሉት ፕ/ር በየነ ኢሶዴፓ ከመድረክ ሙሉ ለሙሉ መውጣቱን ገልጸዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ድረስ ሕጎችን በማርቀቅና በማስተቸት እንዳሳተፋቸው የሚያነሱት ፕ/ር በየነ ቦርዱን የማመን ጉዳይ በተግባር እንደሚታይ ተናረዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ከእስካሁን ታሪኩ በተሻለ መልኩ አሁን ላይ ጥሩ የሚባል ስራ መስራቱንና በተሻለ መንገድ እያሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እና ቦርዱ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ያነሱት ፕ/ር በየነ ጥሮስ ፣ ዕጩ ተወዳዳሪ የመንግስት ሰራተኞች ያለደመወዝ ፈቃድ ወስደው ምርጫ እንደሚቀሰቅሱ በቦርዱ የተገለጸው በእርሳቸው ግምገማ ትክክል እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ ፕ/ር በየነ ሶስት ወር ሊወሰድ በሚችል ቅስቀሳ ይህ መሆን እንደሌለበት ይናገራሉ፡፡ “በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለደመወዝ ፈቃድ ወስዶ እንዴት አድርጎ ነው የሚኖረው ያ ሰው፤ ቤተሰቡን ፣ልጆቹን ምንድነው የሚያረጋቸው? በኢህአዴግ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ተነጋግረን ነበር፤ አሁን ደግሞ እንዴት ያኔ ከነበረው አንሳችሁ ትገኛላችሁ ብለናል ፤ ብዙ ክርክሮች አሉ፤ ስለዚህ በዚህ መንገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይወዳደሩ ነው እንደ ብለን የቀለድንበት ጊዜ አለ” ሲሉ ይህ ድንጋጌ ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡
የምርጫ 2013 ሥጋትና ፈተናዎች
የፊታችን ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 የሚደረገውን ምርጫ እስካሁን ከተካሄዱት ምርጫዎች የተሻለ ለማድረግ ዕድል እንዳለ የሚያነሱት ፕ/ር በየነ ያለፉትን አራት ምርጫዎች “ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ” አይነት ፈተና እንደነበሩ ይገልጻሉ፡፡
እንደ ፕ/ር በየነ ገለጻ ኢህአዴግ ሀገሪቱን በሚመራበት ወቅት ምርጫ ማለት ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል፡፡ በዚህም መሰረት ምርጫው ውስጥ መግባት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ መግባት እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የተሻለ ምርጫ እንደሚደረግ ያላቸውን ተስፋ ያነሱት የኢሶዴፓው ሊቀመንበር ፣ ለዚህም ከገዢው ፓርቲ ቃል እየተገባ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ፕ/ር በየነ ምርጫ ቦርድ ያሳያቸው ምልክቶች በአመዛኙ መልካም እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡ “ከ 1997 ምርጫ በኋላ ያየነው ሁኔታ እንዲደገም የሚፈልጉ ወገኖች ካሉ እዛ ላይ ስጋት ይኖረኛል” የሚሉት ፕ/ር በየነ “ከምርጫው ውጤት በኋላ እኔ አሸንፌ ነበር ፤ የሚባል ነገር ወደ ግጭት ሄዶ ብዙ ዜጎች ተሰውተው ያንንም ሁኔታ ለማረጋጋት ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ከገቡት የፖለቲካ መሪዎች መካከል ነኝ“ ብለዋል፡፡ ፓርቲዎች ያለፈው መጥፎ ሁኔታ እንዳይደገም ፣ ለዚህም ዕድል እንዳይሰጡ ጥሪም አቅርበዋል፡፡ ይህን ምርጫ የማሸነፍና ያለማሸነፍ ጉዳይ “የዓለም መጨረሻ አይደለም” ያሉት ፕ/ር በየነ ኢሶዴፓ ፓርላማ ውስጥ በቂ ወንበሮች ካገኘ በቂያችን ነው ብለዋል፡፡