የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በ10 ከተሞች የዳቦና ዱቄት ፋብሪካዎችን ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ
ፋብሪካዎቹ በ800 ሚሊዮን ብር እንደሚገነቡ ተሰምቷል
ፋብሪካዎቹ ለ1 ሺህ 200 ሰዎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸውም ተብለዋል
የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በ800 ሚሊዮን ብር የዳቦና ዱቄት ፋብሪካዎችን ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ
ጽ/ቤት ቤቱ የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካዎችን ለማስገንባትም ከሚድሮክ ኢንቬስትመንት ግሩፕ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ስምምነቱን ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና የሚድሮክ ኢንቬስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አህመድ ናቸው የፈረሙት፡፡
ፋብሪካዎቹ በሰመራ፣ ጅግጅጋ፣ ሐረር፣ ነቀምት፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ አሶሳ፣ ሐዋሳ፣ ወላይታ ሶዶ እና ቦንጋ እንደሚገነቡም ነው የተገለጸው፡፡የሚገነቡት ፋብሪካዎቹ እያንዳንዳቸው በቀን 400 ኩንታል ዱቄት እና 300 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ይኖራቸዋልም ተብሏል፡፡
ለግንባታ የ1 ዓመት ጊዜ ብቻ የተያዘላቸው ፋብሪካዎቹ የከተሞቹን የዳቦ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለ1 ሺህ 200 ሰዎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩም ይሆናል፡፡
የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በተለይም ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ ዙሮች እየገነባ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ጸ/ቤቱ በተለያዩ ክልሎች ት/ቤቶችን ገንብቷል፤እየገነባም ይገኛል፡፡