የነዳጅ ዋጋ ለሁለተኛ ሳምንት የ3 ዶላር ጭማሪ አሳየ
የቡድን ሰባት አባል ሀገራት በሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብን ተከትሎ የነዳጅ አቅርቦቷን እንደምትቀንስ በመግለጿ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል

ሞስኮ በ2023 የነዳጅ አቅርቦቷን ከ5 እስከ 7 በመቶ እቀንሳለሁ ማለቷ የነዳጅ ዋጋ ይበልጥ እንዳያንረው ተሰግቷል
የነዳጅ ዋጋ በበርሚል የ3 ዶላር ጭማሪ ማሳየቱ ተነገረ።
የአውሮፓ ህብረትና የቡድን ሰባት አባል ሀገራት በሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብን ተከትሎ ሩሲያ የነዳጅ አቅርቦቷን እንደምትቀንስ በማሳወቋ ምክንያት ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት የዋጋ ለውጥ ታይቷል።
ብረንት የተሰኘው ድፍድፍ ነዳጅ በትናንትናው እለት 83 ነጥብ 92 የአሜሪካ ዶላር ተሽጧል።ይህም ከባለፈው ሳምንት የ2 ነጥብ 94 ዶላር ወይንም የ3 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተመዘገበው የነዳጅ ዋጋ ከጥቅምት ወር 2022 ወዲህ ከፍተኛው ስለመሆኑም ሮይተረስ ዘግቧል፡፡
የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ኖቫች ሞስኮ በ2023 የነዳጅ አቅርቦቷን ከ5 እስከ 7 በመቶ እንደምትቀንስ መናገራቸውን የሩስያው የዜና ወኪል አር አይ ኤ ዘግቧል።
በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት በሩሲያ ላይ በአውሮፓ ህብረትና በበለጸጉት ሀገራት የሚጣለው ማዕቀብ የሚቀጥል ከሆነም አቅርቦቱ ዝቅ ሊል እንደሚችል ተገልጿል።
አቅርቦቱ እየቀነስ ከሄደ የነዳጅ ዋጋ ከዚህም ሊያሻቅብ እንደሚችል አር ጄ ኦ ፉውቸርስ የተሰኘ ተቋም ከፍተኛ የገበያ ስትራቴጂስት ኢሊ ተስፋዬ ይናገራሉ።
አቅርቦቱ የቀነሰበት ወቅት አውሮፓውያን የነዳጅ ፍላጎታቸው የሚጨምርበት መሆኑም የነዳጅ ዋጋ በበርሚል ከ80 ዶላር በታች እንዳይወርድ ያደርገዋልም ነው የሚሉት።
በአሜሪካም በቴክሳስ እና ኖርዝ ዳኮታ የሚገኙ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያዎች ስራ የሚያቆሙበት ወቅት መሆኑን የሚያነሱ ባለሙያዎች የዋጋ ጭማሪው ቀጣይ እንደሚሆን ስጋታቸውን ያጋራሉ።
የሩስያ የነዳጅ አቅርቦት መቀነስና በቻይና የኮቪድ 19 ዳግም መቀስቀስ የሚያመጣው የእንቅስቃሴ ገደብ የነዳጅ ዋጋን በበርሚል እስከ 100 ዶላር ሊያደርሰው እንደሚችል ጆቫኒ ስታውኖቮ የተባሉ ተንታኛ ገልጸዋል።
10 ወራት ያስቆጠረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የነዳጅ ዋጋን እንዲጨምር ማድረጉን ቀጥሏል።