ቬንዙዌላ ከተቃዋሚዎች ጋር መደራደሯን ተከትሎ አሜሪካ የጣለችውን የነዳጅ ማዕቀብ አቃለለች
ስምምነቱ በቬንዙዌላ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊቀንስ እንደሚችል ያበሰረ ነው ተብሏል
የዓለም ትልቁ የነዳጅ ክምችት ያላት ቬንዙዌላ እርምጃው እንደገና ወደ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ እንድትገባ ያስችላታል
የኒኮላስ ማዱሮ መንግሥት እና የቬንዙዌላ ተቃዋሚዎች ፖለቲካዊ አለመግባባትን ለመስበር ማኅበራዊ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሯል።
ይህን ተከትሎም የአሜሪካ መንግሥት ትላልቅ የሀገሪቱ የነዳጅ ኩባንያዎች በቬኔዙዌላ ውስጥ ሥራቸውን እንዲጀምሩ በመፍቀድ ምላሽ ሰጥቷል።
ስምምነቱ በቬንዙዌላ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊቀንስ እንደሚችል ያበሰረ ነውም ተብሏል።
ስምምነቱ የማዱሮ መንግስት የታሰሩ ንብረቶችን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመተማመን ፈንድ እንዲቆጣጠር መንገድ እንደሚከፍት ተነግሯል።
በዚህ ስምምነት ተመድ ለትምህርት፣ ጤና፣ የምግብ ዋስትና፣ የጎርፍ ምላሽ እና ኤሌክትሪክ ጋር የተያያዙ ፕሮግራሞችን ጨምሮ በደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ለተለያዩ ማህበራዊ ፕሮጀክቶች የሚውል ፈንድ እንዲቆጣጠር ያደርጋል ነው የተባለው።
ድርድሩን ያመቻቸው የኖርዌይ ልዑክ አባል ዳግ ኒላንደር “በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ የቬንዙዌላ ሀብቶችን ለይተናል፤ አሁን ማንቀሳቀስ ይቻላል” ብለዋል።
ምን ያህሉ የሀብት መጠን እንደሚለቀቅ አልተገለጸም ሲል ናሽናል ኒውስ አጃንስ ፍራንስ ፕረስን ጠቅሶ ዘግቧል።
በሜክሲኮ የተፈረመው ስምምነት በሁለቱ ወገኖች መካከል ለ15 ወራት የዘለቀው አለመግባባት እልባትም የሰጠ ነው ተብሏል። ይህም ከቬንዙዌላ ወደ ቀጣናው የሚደርሰውን ከፍተኛ የስደተኞች ፍሰት በማቃለል እና የዓለም የነዳጅ ገበያዎችን ሳይቀር እንደሚያረጋጋ ተስፋ ተጥሎበታል።
ፕሬዝዳንት ኒኮላ ማዱሮ ስምምነቱን በትዊተር ገፃቸው አወድሰውታል። “ለቬንዙዌላ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል፣ ሁሉም የቬንዙዌላ ዜጎች ወደሚፈልጉት ሰላም እና ደህንነት ለመጓዝ የሚያስችል መንገድ ይከፍታል” ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ እንዳሉት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ፓርቲዎቹን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን በመግለጽ ግኝቱን “ለቬንዙዌላ ህዝብ ሰፊ ጥቅሞችን መስጠት የሚያስችል ጠቃሚ ምዕራፍ ነው” ሲሉ ገልጸዋል ።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ስምምነቱ በቬንዙዌላ ዲሞክራሲን ወደነበረበት ለመመለስ አስፈላጊ እርምጃዎችን የሚያመለክት ነው ያለ ሲሆን የሀገሪቱ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ኩባንያ የተገደበ የነዳጅ ማውጣት ስራዎችን እንዲቀጥል ፍቃድ ሰጥቻለሁ ብሏል።።
ፈቃዱ ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር የማዱሮ መንግስት በስምምነቱ የገባውን ቃል ማሟላቱን ይገመግማል ሲል ግምጃ ቤቱ ተናግሯል።
በዓለም ትልቁ የነዳጅ ክምችት ባላት ቬንዙዌላ ውስጥ ያለው የአሜሪካው ቼቭሮን የኃይል ኩባንያ እረፍት ማግኘቱ አገሪቱ እንደገና ወደ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያዎች እንድትገባ ያስችላታል ተብሏል።
ከሩሲያና ዩክሬንን ጦርነት በኋላ በዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ላይ ከደረሰው ጫና ተከትሎ የቬንዙዌላን ችግር ለመፍታት ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።