የአውሮፓ ህብረት የሩሲያ አንድ በርሜል ነዳጅ ከ60 ዶላር በላይ እንዳይሸጥ ወሰነ
ሩሲያ በበኩሏ በውሳኔው ለተሳተፉ ሀገራት ነዳጇን እንደማትሸጥ አስታውቃለች
የአውሮፓ ህብረት የሩሲያ ነዳጅን ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ በሚገዙ ሀገራት እና ኩባንያዎች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል
የአውሮፓ ህብረት የሩሲያ አንድ በርሜል ነዳጅ ከ60 ዶላር በላይ እንዳይሸጥ ወሰነ።
የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት አቋርጣ እንድትወጣ ተጽእኖ የሚያደርጉ ጫናዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል።
የሩሲያ ነዳጅ ለሞስኮ ጦር ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው የሚለው የአውሮፓ ህብረት ጦርነቱን ተከትሎ በነዳጅ እጥረቱ እየተፈተነም ይገኛል።
ህብረቱ የነዳጅ እጥረቱን ለመከላከል እና ሩሲያ ከነዳጅ ሽያጭ የምታገኘውን ገቢ ለመቀነስ በሚል የሩሲያ ነዳጅ አንድ በርሜል ከ60 ዶላር በላይ እንዳይሸጥ መወሰኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
- የሩሲያ ነዳጅ በድብቅ ወደ አውሮፓ ገበያዎች እየገባ እንደሆነ ተገለጸ
- “ያለ ሩሲያ ጋዝና ነዳጅ እንዴት መቀጠል ይቻላል” የሚለው የአውሮፓ ሀገራትን ማሳሰቡ ተገለፀ
ህብረቱ የወሰነውን የነዳጅ ሽያጭ ተመን በሚጥሱ ሀገራት እና የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድም ተገልጿል።
ሩሲያ በበኩሏ የአውሮፓ ህብረት የወሰነውን የነዳጅ ሽያጭ ተመን እንደማትቀበል አስታውቃለች።
የክሪምሊን ቤተ መንግስት ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ እንዳሉት ሩሲያ የአውሮፓ ህብረት የሩሲያ ነዳጅ መሸጫ ተመን ለወሰኑ ሀገራት እና ውሳኔውን ለተቀበሉ ሀገራት ነዳጇን እንደማትሸጥ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ነዳጅ መሸጫ ተመን ውሳኔን እየመረመረች መሆኗን፣ በቀጣይ ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያም እያሰበችበት እንደሆነም ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።
ሩሲያ አሁን ላይ አንድ በርሜል ነዳጅን በ67 ዶላር በመሸጥ ላይ ስትሆን ቻይና፣ ሕንድ፣ አውሮፓ እና ሌሎች የእስያ ሀገራት ነዳጇን የምትሸጥላቸው ሀገራት ናቸው።
አስር ወራት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋን ከማናሩ ባለፈ የዓለምን ዲፕሎማሲም እየፈተነ ይገኛል።