የሩሲያን ነዳጅ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ መተካት እንደማይቻል የዓለም ባንክ አስታወቀ
የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ነዳጅ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ባንዴ ማቆም ብዙ ጉዳት ያስከትላልም ተብሏል
ሩሲያ 40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን ነዳጅ ፍላጎት ትሸፍናለች
የሩሲያን ነዳጅ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ መተካት እንደማይቻል የዓለም ባንክ አስታወቀ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ከገቡ ሰባት ወር ሆኗቸዋል።
ሩሲያ ለልዩ ዘመቻ በሚል ጦሯን ወደ ዩክሬን ማዝመቷን ተከትሎም ሞስኮ ነዳጇን ወደ አውሮፓ ሀገራት እንዳትሸጥ ማዕቀብ ተጥሎባታል።
በማዕቀቡ ምክንያትም ሩሲያ ነዳጇን ወደ አውሮፓ ልካ መሸጥ ባለመቻሏ በሩሲያ ነዳጅ ላይ ጥገኛ የነበሩ ሀገራት ለችግር ተዳርገዋል።
የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ የሩሲያ ነዳጅን ለመተካት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ሲሆኑ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ መወሰድ ስላለበት እርምጃ ምላሽ ሰጥተዋል።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ የአውሮፓ ሀገራት ከሌሎች ሀገራት ነዳጅ ለማግኘት እያደረጉት ያለው ጥረት ጥሩ ቢሆንም የሩሲያን ነዳጅ በአጭር ጊዜ መተካት አይቻልም ማታቸውን ከሲቢኤስ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ላይ ተናግረዋል።
ሩሲያ ከጦርነቱ በፊት 40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን ነዳጅ ፍላጎት የምትሸፍን ሲሆን በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት ነዳጅ እና የምግብ ዋጋ በአውሮፓ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አያሻቀበ ይገኛል።
አውሮፓዊያን ቀስ በቀስ ከሩሲያ ነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ ያሳሰቡት የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ባንዴ ነዳጅ ከሩሲያ ላለመግዛት መሞከር ብዙ የኢኮኖሚ ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።
በአውሮፓ የነዳጅ እጥረት መፈጠሩን ተከትሎ በርካታ ዜጎች መንግስት የኢኮኖሚ ድጎማዎችን እንዲያደር በሰላማዊ ሰልፍ እና በስራ ማቆም አድማ በመጠየቅ ላይ ሲሆኑ ሀገራትም የነዳጅ ድጎማ በጀት በመፈለግ ላይ ናቸው።
ለአብነትም ጀርመን፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ሆላንድ እና ሌሎች ሀገራት ቢሊዮኖችን በመመደብ ላይ ሲሆኑ ጀርመን 200 ቢሊዮን ዩሮ፣ ብሪታንያ 150 ቢሊዮን እንዲሁም ፈረንሳይ 160 ቢሊዮን ዩሮ ለነዳጅ ድጎማ በመበጀት ላይ መሆናቸውን አሳውቀዋል።