የነዳጅ ዋጋ የ5 በመቶ ጭማሪ አሳየ
የነዳጅ ላኪ ሀገራት ማህበር (ኦፔክ) አባላት እለታዊ የነዳጅ አቅርቦታቸውን መቀነሳቸው በእስያ የነዳጅ ዋጋን እንዲጨምር ማድረጉ ተነግሯል
የኦፔክ አባል ሀገራት በጠቅላላ በየቀኑ ለአለም ገበያ ከሚያቀርቡት ነዳጅ ላይ የ2 ሚሊየን በርሚል ቅናሽ ለማድረግ ተስማምተዋል
የነዳጅ ዋጋ ዳግም ጭማሪ ማሳየት መጀመሩ ተነገረ።
በእስያ ብሬንት የተሰኘው ድፍድፍ ነዳጅ በበርሚል በ84 የአሜሪካ ዶላር እየተሸጠ ነው።
ይህም ከሰሞኑ የ4 ዶላር ወይም የ5 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
ለጭማሪው ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰውም የነዳጅ አምራችና ላኪ ሀገራት ማህበር (ኦፔክ) አባላት ትናንት ያሳለፉት የነዳጅ አቅርቦትን የመቀነስ ውሳኔ ነው’’
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት እንደተጀመረ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ የነበረው የነዳጅ ዋጋ ወደቀደመ ዋጋው ተመልሶ ነበር።
አሜሪካም ነዳጅ አቅራቢ ሀገራት ምርታቸውን በማሳደግ ዋጋውን ለማረጋጋት እንዲሰሩ ጥሪ ስታደርግ ቆይታለች።
የአለም የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት አቅርቦትን 40 ከመቶ የሚሸፍኑት የኦፔክ አባል ሀገራት ትናንት ባካሄዱት ስብሰባ ግን ዋጋውን ይበልጥ ለማረጋጋት በየቀኑ የሚያቀርቡትን ነዳጅ መጠን ለመቀነስ ተስማምተዋል ብሏል የሳኡዲ ብሄራዊ የዜና አገልግሎት።
ሀገራቱ በድምሩ በቀን ውስጥ ከሚያቀርቡት ነዳጅ 2 ሚሊየን በርሚል ለመቀነስ ነው የተስማሙት።
ክዚህ ውስጥ ሳኡዲ አረቢያ 500 ሺህ፣ ኢራቅ 211 ሺህ በርሚል ነዳጅ ይቀንሳሉ የተባለ ሲሆን፥ አረብ ኤምሬትስ፣ ኩዌት፣ አልጀሪያ እና ኦማንም አቅርቦታቸውን እንደሚቀሱ ተገልጿል።
አሜሪካ ይህን የኦፔክ አባል ሀገራት ውሳኔ “የማይመከርና የነዳጅ ዋጋን የማያረጋጋ” ነው በሚል ተቃውማዋለች።