ሩሲያ ነዳጇን ወደ ምስራቅ አውሮፓ እና እስያ ማዛወሯን አስታውቃለች
አሜሪካ የአውሮፓ ነዳጅ ፍላጎትን በመሸፈን ቀዳሚዋ ሀገር ሆነች።
ለአንድ ሳምንት በሚል የተጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን በአውሮፓ እና በዓለም የኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲ አሰላለፎች ላይ ለውጥ አስከትሏል።
ሩሲያ ጦሯን ወደ ዩክሬን ከመላኳ በፊት የአውሮፓ 40 በመቶ ነዳጅ ፍላጎትን ትሸፍን የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 19 በመቶ ዝቅ ብሏል።
- ሩሲያ፥ ማዕቀብ የተጣለበትን የነዳጅ ምርቷን ወደ ወዳጅ ሀገራት መላኬን ቀጥያለሁ አለች
- የሩሲያን ነዳጅ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ መተካት እንደማይቻል የዓለም ባንክ አስታወቀ
ጦርነቱን ተከትሎ አውሮፓ እና አሜሪካ በሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ እና የዋጋ ተመን ማውጣታቸውን ተከትሎ ሞስኮ በአውሮፓ የነበራት የነዳጅ ገበያ ዝቅ ማለቱን ሲኤንኤን ዘግቧል።
አሜሪካ አሁን ላይ 31 በመቶ የአውሮፓ ነዳጅ ፍላጎትን በመሸፈን ላይ ስትሆን ኖርዌይ እና ካዛኪስታን ደግሞ በቅደም ተከተል የአውሮፓ ነዳጅ ገበያን በመቆጣጠር ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል።
ሩሲያ አሁንም ቀላል የማይባል መጠን ነዳጅ ለአውሮፓ በማቅረብ ላይ ስትሆን አብዛኛውን የነዳጅ ምርት ግን ለቻይና ፣ ሕንድ እና ሌሎች የእስያ ሀገራት በማቅረብ ላይ መሆኗን አስታውቃለች።
ሞስኮ ነዳጇን ለአውሮፓ ገበያዎች አንድ በርሜል ነዳጅን በ54 ዶላር የምትሸጥ ሲሆን በዓለም አቀፍ ገበያ ግን አንድ በርሜል ነዳጅ በ78 ዶላር በመሸጥ ላይ ይገኛል።
ይሁንና አውሮፓ የአሜሪካንን እና ሌሎች ሀገራትን ነዳጅ በውድ ዋጋ ለመግዛት መገደዱን የአውሮፓ መረጃዎች ማዕከል አስታውቋል።
ሩሲያ በተለይም የነዳጅ ዋጋ ተመን ለጣሉ ሀገራት ነዳጇን እንደማትሸጥ የገለጸች ሲሆን የቡድን ሰባት ሀገራት ግን ሞስኮ ነዳጇን በበርሜል ከ60 ዶላር በላይ እንዳይሸጥ ወስነዋል።