ኡጋንዳ የመጀመሪያውን የነዳጅ ቁፋሮ ስራ ጀመረች
ኡጋንዳ በአራት ቢሊዮን ዶላር የምስራቅ አፍሪካ ድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ልትገነባ መሆኑም ተገልጿል
ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ፤ በቀን 40 ሺህ በርሜል ነዳጅ ያመርታል የተባለውን የኪንግፊሸር የነዳጅ ስፈራ ቁፋሮን በይፋ አስጀምረዋል
ኡጋንዳ የመጀመሪያውን የነዳጅ ቁፋሮ ስራ ጀመረች
ኡጋንዳ ከዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ማግኘቷ ይታወቃል፡፡
በዚህም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በተገኙበት በአልበርት ሀይቅ "ኪንግ ፊሸር" የነዳጅ ስፍራ የመጀመሪያ ነው የተባለለት የነዳጅ ቁፋሮ ስራን በይፋ ጀምራለች፡፡
ይህም ምስራቅ አፍሩካዊቷ ሀገር ኡጋንዳ ነዳጅን በማውጣት የጥቁር ወርቅ (ነዳጅ) አምራች የሆኑ ሀገራት ጎራን ለመቀላቀል እየተንደረደረች ለመሆኗ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
የኡጋንዳ የነዳጅ ባለስልጣን፤ ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በ2025 "በቀን 40 ሺህ በርሜል ነዳጅ ያመርታል የተባለውን በኪንግፊሸር የነዳጅ ስፈራ ቁፋሮን በይፋ አስጀምረዋል" ሲል በትዊተር ገጹ አስታውቋል፡፡
የነዳጅ ቁፋሮው የሚከናወነው በቻይናው ኩኖክ ኩባንያ መሆኑም ገልጿል ባለስልጣኑ፡፡
የኡጋንዳ ኢነርጂ ሚንስትር ሩት ናንካቤሩአ በበኩላቸው "እንደ ሀገር ተደስተናል፤ ለአፍሪካም በተመሳሳይ" ብለዋል፡፡
በኡጋንዳ እና ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ መካከል ባለውን የተፈጥሮ ድንበር የሚገኘው አልበርት ሃይቅ በግምት 6.5 ቢሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ እንዳለው ይታመናል፡፡ ከዚህ የነዳጅ መጠን 1.4 ቢሊዮን በርሜሎች አሁን ማግኘት እንደሚቻልም ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ኡጋንዳ የነዳጅ ቁፋሮዋን እውን ካደረገች በያዝነው የ2023 በጀት ዓመቱ ውስጥ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በ 5.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተጨመሪም የኡጋንዳ መንግስት አራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ የምስራቅ አፍሪካ ድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት ማቀዱን በካምፓላ የሚታተመው "ዴይሊ ሞኒተር" ጋዜጣ በቅርቡ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
ፕሮጀክቱ 1 ሺህ 443 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የነዳጅ ቦይ ከኡጋንዳ ወደ ታንዛኒያ ታንጋ ወደብ ለማልማት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ይሁን እንጅ እምቅ ነዳጅ ኃብቷን በመጠቀም ትልቁን አልማ እድገቷን ለማሳለጥ ያቀደችው ኡጋንዳ የያዘችውን ፕሮጀክት ከወዲሁ ትችት በማስተናገድ ላይ ነው፡፡
የአካባቢ ተሟጋቾች እና የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በህንድ ውቅያኖስ ላይ ካለው የታንዛኒያ ወደብ ጋር የሚያገናኘውን ረጅሙን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት እየተቃወሙት ናቸው፡፡
ዋና ምክንያታቸው ደግሞ መስመሩ በርካታ ብሔራዊ ፓርኮችን እና የተፈጥሮ ሀብቶችን አቋርጦ የሚያልፍ መሆኑ በተፈጥሮ ላይ የራሱ ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀርም የሚል ነው ተብሏል፡፡