በቴ ኡርጌሳ በትወልድ ከተማው መቂ መገደሉን አገኘሁት ባለው መረጃ ማረጋገጡን ኦነግ ገልጿል
ኦነግ የበቴ ኡርጌሳ ግድያ በገለልተኛ አካል እንዲመረመር ጠየቀ።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(አነግ) ባወጣው መግለጫ በአባሉ በቴ ኡርጌሳ ላይ የደረሰው "ዘግናኝ ግድያ" በገለልተኛ አካል እንዲመረመር ጠይቋል።
በቴ ኡርጌሳ በትውልድ ከተማው መቂ መገደሉን አገኘሁት ባለው መረጃ ማረጋገጡን ኦነግ ገልጿል።
የፖሊቲካ ኦፊሰር በሆነው አባሉ በቴ ላይ ተፈጽሟል ያለው ዘግናኝ ግድያ ጥልቅ ሀዘን ውስጥ እንዳስገባው የገለጸው ኦነግ በነቁ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና በታዋቂ ሰዎች ላይ የሚደረገው ግድያ ቀጥሏል ብሏል።
ኦነግ የታዋቂው አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ሳይረሳ እና ቤተሰቦቹ ፍትህ ሳያገኙ፣ የበቴን ግድያ መስማት አሳዛኝ ነው ሲል ገልጿል።
ሁኔታዎች አስቸጋሪ ቢሆኑም በግድያው ላይ ተጨማሪ ምርመራ ይደረጋል ብሏል ኦነግ።በቴ ኡርጌሳ በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ አባል ነው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል ባለስልጣናት "ፈጣን፣ገለልተኛ እና ሙሉ" ምርመራ አድርገው ግድያውን የፈጸሙትን ተጠያቂ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በቴ በቅርቡ ከፈረንሳያዊ ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊኖዶ ጋር ቃለ መጠይቅ ማድረጉን ተከትሎ ከጋዜጠኛው ጋር በፖሊስ ታስሮ ነበር።
ጋዜጠኛው ብዙም ሳይቆይ ተፈትቶ ወደ ሀገሩ የሄደ ሲሆን በቴ ቆይቶ በዋስ መፈታቱ ይታወሳል።