ኦማን ዜጎቿ የውጭ ሀገራት ዜጎችን እንዲያገቡ ፈቀደች
የመካከለኛዋ ምስራቅ ሀገር ኦማን የህዝብ ብዛቷ ከአራት ሚሊዮን በታች ነው
ኦማን ከፈረንጆቹ 1993 ጀምሮ የሀገሪቱ ዜጎች የውጭ ዜጎችን ለማግባት ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያሟሉ ግዴታ ጥላ ነበር
ኦማን ዜጎቿ የውጭ ሀገራት ዜጎችን እንዲያገቡ ፈቀደች።
የመካከለኛው ምስራቋ ኦማን በፈረንጆቹ 1993 ላይ ነበር ዜጎቿ የውጭ ሀገራት ዜጎችን እንዳያገቡ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠችው።
ይህን ተከትሎ የሀገሪቱ ዜጎች ህጉን ሲቃወሙ ቆይተዋል የተባለ ሲሆን በ2020 ወደ ስልጣን የመጡት ሱልጣን ሀይታም ቢን ታሪክ የተለያዩ ለውጦችን እንደሚያመጡ ቃል ገብተው ነበር።
ከሚያሻሽሏቸው ህጎች መካከልም የኦማን ዜጎች የሌላ ሀገር ዜጋ እንዳያገቡ የሚከለክለውን አልያም ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚደነግገውን ህግ ከያዝነው ወር ጀምሮ መሻሩን ተናግረዋል።
እንደ ኦማን ዜና አገልግሎት ዘገባ ከሆነ የሀገሪቱ ዜጎች የማንንም ፈቃድ ሳይጠይቁ የፈለጉትን ሀገር ዜጋ የማግባት መብት የሚሰጥ አዋጀህ 2023 የተሰኘ ህግ ጸድቋል።
በዚህ ህግ መሰረት ከዚህ በፊት ስራ ላይ ይውል የነበረው አዋጅ 89/1993 እና ኦማናዊያን የውጭ ሀገራትን ለመግባት ከፈቀዱ ማሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎችን ይዘረዝር የነበረው ህግ ተሽሯል ተብሏል።
አዲሱ የኦማን ህግ ዜጎች መብታቸውን የበለጠ እንዲጠቀሙ ከማድረጉ ባለፈ የውጭ ሀገራት ወደ ኦማን መጥተው ኢንቨስት ኢንዲያደርጉ እና ንግድን የሚያሻሽል እንደሆነም ተገልጿል።
የኦማን የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ዜጎች ጋብቻቸው እንዲጸድቅላቸው የመጠየቅ እና ማስረጃ የማግኘት መብቶችን ሰጥቷል።
ሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኦማን በአዲሱ ህግ መሰረት ዜጎች ጋብቻ ሲፈጽሙ የእስልምና ህግን የመከተል ግዴታን ጥሏል።