ከ69 ሰዎች አንዱ በጦርነትና ግጭት ከቀየው ተፈናቅሏል - ተመድ
የተፈናቃዮች ቁጥር ከአስር አመት በፊት ከነበረበት በእጥፍ ጨምሮ 120 ሚሊየን ደርሷል ተብሏል
የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን አዲስ ሪፖርቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል
ከአለማችን ህዝብ 1.5 በመቶው በሃይል ከቀየው ለመፈናቀል መገደዱ ተገለጸ።
የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ዛሬ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያመላክተው በአለማቀፍ ደረጃ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በ2023 117.3 ሚሊየን ደርሷል።
ይህም ከ69 ሰዎች አንዱ ግጭትና ጦርነትን አልያም የሰብአዊ መብት ጥሰትን ሽሽት ከቀየው ለመፈናቀል መገደዱን ያመላክታል።
ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው የተፈናቃዮች ቁጥር በ2014 ከነበረበት በእጥፍ የጨመረ ሲሆን በሚያዚያ ወር 2024ም 120 ሚሊየን ደርሷል።
በ2023 ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 8 ነጥብ 8 ሚሊየን እንደነበር ያነሳው ሪፖርቱ፥ የዩክሬን እና ሱዳን ጦርነት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ አብራርቷል።
ባለፈው አመት 117.3 ሚሊየን ከደረሰው የተፈናቃዮች ቁጥር 68.3 ሚሊየኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ናቸው የተባለ ሲሆን፥ ድንበር አቋርጠው በተለያዩ ሀገራት በስደት የሚገኙት ቁጥር 43.4 ሚሊየን መድረሱን የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ገልጿል።
በሀገራቸው ግድያ እና እስርን ፈርተው በሌሎች ሀገራት ጥገኝነት የጠየቁ ሰዎች ቁጥርም ከ2022ቱ በ26 በመቶ ጨምሮ 6.9 ሚሊየን መድረሱም ነው የተጠቆመው።
ከጣሊያን ህዝብ በእጥፍ የሚበልጠው የተፈናቃዮች ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ መሄዱ አሳሳቢ ነው ያሉት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዴ ሀገራት ዜጎቻቸውን የሚያፈናቅሉ መንስኤዎችን ለይተው በፍጥነት መፍትሄ እንዲያበጁ አሳስበዋል።
ከአጠቃላይ ተፈናቃዮቹ ውስጥ 20 በመቶውን ሱዳን እና ቻድ ይይዛሉ፤ በጋዛ ከስምንት ወራት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነትም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያንን አፈናቅሏል።
በተለያዩ ሀገራት በስደት ከሚገኙት ውስጥ ሶስት አራተኛው የአፍጋኒስታን፣ ሶሪያ፣ ቬንዙዌላ፣ ዩክሬንና ፍልስጤም ዜጎች መሆናቸውንም ነው ሪፖርቱ ያመላከተው።
የመንግስታት ድርጅት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ የሚገኙ ስደተኞችን ለመጠበቅ በ1951 የስደተኞች ኮንቬንሽን ማውጣቱ ይታወሳል።
በወቅቱ የስደተኞች ቁጥር 2.1 ሚሊየን እንደነበር የሚያስታውሰው ዘ ጋርዲያን፥ በ1980ዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ 10 ሚሊየንን ተሻግሯል ይላል።
በ1980ዎቹ በኢትዮጵያ እና አፍጋኒስታን የተከሰቱ ጦርነቶች የስደተኞችን ቁጥር በ1990 20 ሚሊየን እንዳደረሰውም ነው የሚያወሳው።
የአሜሪካ የአፍጋኒስታን እና ኢራቅ ወረራ ከደቡብ ሱዳን እና ሶሪያ ጦርነት ጋር ተዳምሮ በ2021 የስደተኞችን ቁጥር 30 ሚሊየን አድርሶታል።
በአሁኑ ወቅት የቀጠሉት የዩክሬን፣ ሱዳን እና ጋዛ ጦርነቶች የተፈናቃዮችን ቁጥር በየቀኑ እየጨመሩት ነው ተብሏል።