አሜሪካ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ ልትልክ ነው ተባለ
ጣልያን እና ግሪክ ከላቲን አሜሪካ የሚመጡ ስደተኞችን ለመቀበል ተስማምተዋል
በ2024 ታህሳስ ወር ላይ አሜሪካን ከሜክሲኮ በሚያዋስናት ድንበር 300ሺ ስደተኞች ወደ አሜሪካ ለመግባት ሲጠባበቁ ነበር
በህገወጥ ስደተኞች እና በድንበር ደህንነት ቀውስ ተቸግርያለሁ ያለችው አሜሪካ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ ሀገራት ልትልክ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
አሜሪካ በላቲን አሜሪካ ሀገራት በከፈተቻቸው የስደተኛ ማስተናገጃ ቢሮዎች ጥገኝነት የሚጠይቁ ስደተኞችን ነው ወደ አውሮፓ እልካለሁ ያለችው፡፡
ከባለፈው አመት ጀምሮ በኮሎምቢያ፣ኢኳዶር፣ኮስታሪካ እና ጓቲማላ በከፈተቻቸው ቢሮዎች ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማስተናገድ ላይ የምትገኝው ሀገሪቱ የህገወጥ ስደተኛ ቁጥርን ለመቀነስ በሌሎች የላቲን አሜሪካ ሀገራትም ተመሳሳይ ቢሮዎችን ለመክፈት ውጥን አላት፡፡
ሲቢኤስ ኒውስ የአሜሪካ ሀገር ውስጥ ደህንነት ተቋምን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ዋሽንግተን ከነዚህ ሀገራት የሚመጡ ስደተኞችን ወደ ስፔን እና ግሪክ ለማሻገር ከስምምነት ላይ ደርሳለች፡፡
በሙከራ ደረጃ ግሪክ እና ጣሊያን እያንዳንዳቸው 500 ስደተኞችን ለመቀበል የፈቀዱ ሲሆን በቀጣይ ከአሜሪካ መንግስት ጋር በሚኖራቸው ስምምነት መሰረት ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ተነግራል፡፡
የጆ ባይደን አስተዳደደር ከዚህ ቀደም ከካናዳ እና ስፔን ጋር በደረሰው ስምምነት ስደተኞችን ወደ ሀገራቱ መላክ የጀመረ ሲሆን ከሌሎች ሀገራት ጋርም ተመሳሳይ ሰምምነትን ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ሰአት በ4 የላቲን አሜሪካ ሀገራት በተከፈቱ የስደተኛ ቢሮዎች ከ10ሺ በላይ አመልካቾች ይገኛሉ፡፡
በፖለቲካዊ እይታቸው፣ በሚከተሉት ሃይማኖት እና በሌሎችም ጉዳዮች ጫና የሚደርስባቸው ስደተኞች ቅድሚያ የሚያገኙ ይሆናል፡፡
ሆኖም እቅዱን የሚቃወሙ ድምጾች ከአሁኑ እየተሰሙ ይገኛሉ። ስፔ፣ ጣሊያን እና ግሪክ በሜድትራኒያን በኩል በሚመጡ አፍሪካዊያን ህገ ወጥ ስደተኞች የሚጨናነቁ መሆናቸውን በማንሳት ያለብን ችግር ይበቃናል የሚሉ ድምጾች ስደተኞች ይላኩባቸዋል ከተባሉት ሀገራት ዜጎች ተደምጠዋል፡፡
በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጠበቅ ብለው የነበሩ የስደተኛ ፖሊሲዎችን የአሁኑ አስተዳደደር በማላላት ላይ ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎም አሜሪካ ከ2021 የመጀመርያ ወር ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የስደተኞች ቁጥርን በድንበሯ እያስተናገደች ትገኛለች ፡፡
በተያዘው አመት ታህሳስ ወር ላይ ብቻ 300ሺ ስደተኞች ድንበር ለማቋረጥ ሲጠባበቁ የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የተባለው ነው፡፡
ላቲን አሜሪካ ከሚባሉት ሀገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህገወጥ ስደተኞችን የምታስተናግደው ዋሽንግተን አዲስ በቀየሰችው መንገድ ህገ ወጥ ስደተኞችን ለመቀነስ ብትወጥንም በአካባቢው ያለው ያልተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ለእቅዱ መሳካት ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ባለፉት አስርተ አመታት ከቬንዚዌላ ብቻ በሀገሪቱ ያለውን የኢኮኖሚ ውድቀት ሽሽት 8 ሚልየን ዜጎች ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡
ከነዚህ መካከል አብዛኞቹ ወደ ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጥገኝነት ሲጠይቁ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ወደ አሜሪካ ድንበር ለመሻገር አደገኛ የሚባሉ የህገወጥ መንገዶችን ይጠቀማሉ።