ለሸንቃጣ ሴቶች ብቻ አገልግሎት እሰጣለሁ ያለው ጂም ቤት
ጂም ቤቱ በወሰደው እርምጃ ምክንያት ዋነኛ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ ሆኗል
የስፖርት ቤቱ እድሜያቸው ከ30 በላይ የሆኑ ሴቶች ጊዜያቸውን ልብስ በመቀየር እና ሰው በማማት እያሳለፉ ነው ብሏል
ለሸንቃጣ ሴቶች ብቻ አገልግሎት እሰጣለሁ ያለው የደቡብ ኮሪያ ጂም ቤት
በደቡብ ኮሪያ መዲና ሲሴኡል አቅራቢያ ኢንቺዮን ከተማ ያለ አንድ የስፖርት ወይም ጂም ቤት ከሰሞኑ የወሰደው እርምጃ በርካቶችን አነጋግሯል፡፡
ይህ ስፖርት መስሪያ ቤት በተለምዶ አጁማስ የሚባሉ ሴቶች ያልተገባ ድርጊት እያደረጉ ስራዬን እየጎዱብኝ ነው በሚል እድሜያቸው ከ30 በላይ የሆኑ ሴቶችን አግዷል፡፡
በደቡብ ኮሪያ እቃ መስረቅን ጨምሮ ያልተገባ ድርጊት እና ባህሪ ያላቸው ሴቶች አጁማስ የሚል ስያሜ በማህበረሰቡ ተሰጥቷቸዋል፡፡
እንደ ደቡብ ኮሪያ ዜና ወኪል (ዮናሀፕ) ዘገባ ከሆነ ስሙ ያልተጠቀሰው ይህ ጂም ቤት አጁማስ የሚባሉ ሴቶች ወደ ጂሙ ከገቡ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉት ስፖርት ሳይሰሩ ነው ብሏል፡፡
እነዚህ ሴቶች ወደ ጂም ቤት ከገቡ በኋላ ልብስ በመቀየር፣ ጥሩ የሰውነት አቋም ስላላቸው ወጣት ሴቶች በማውራት፣ እቃዎችን በማንሳት እና ሌሎች ልተገቡ ድርጊቶችን እንደሚያደርጉም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ወጣት ሴቶቹም በሚያዩት ነገር በመበሳጨት ከጅም ቤቱ እየቀሩ ነው የተባለ ሲሆን በመጨረሻም ይህ ጅም ቤት በተለምዶ አጁማስ ተብለው የሚጠሩ ሴቶችን አግዷል፡፡
ጉዳዩ በደቡብ ኮሪያ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን የጅም ቤቱ እርምጃ በሴቶች ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው፣ አጥፊዎችን ለይቶ መቅጣት እየተቻለ የተወሰደው ድርጊት ግን ስህተት ነው ተብሏል፡፡
በጅም ቤቱ ላይም የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ የተጀመረበት ሲሆን ስፖርት መስሪያ ቤቱ ወይም ጂም ቤቱ እርምጃውን የወሰደው ቢዝነሱ እንዳይጎዳበት በሚል ከመሆኑ ውጪ የሴት ጥላቻ እንደሌለበት አስታውቋል፡፡