ኢለን መስክ ቻትጅፒቲን ለመግዛት ያቀረበው የ97 ቢሊዮን ዶላር ጥያቄ ውድቅ ተደረገ
የቴክኖሎጂው እናት ኩባንያ ኦፕን አይ የኢለን መስክን ጥያቄ እንደማይቀበል ገልጿል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/15/258-123149-whatsapp-image-2025-02-15-at-11.31.36-am_700x400.jpeg)
ኢለን መስክ ከኦፕን አይ መስራቾች መካከል አንዱ ነበሩ
ኢለን መስክ ቻትጅፒቲን ለመግዛት ያቀረበው የ97 ቢሊዮን ዶላር ጥያቄ ውድቅ ተደረገ፡፡
አሁን ላይ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሆኑት ኢለን መስክ ከ10 ዓመት በፊት ከሌሎች ወዳጆቻቸው ጋር በመሆን ነበር ኦፕን አይ የተሰኘውን ኩባንያ ያቋቋሙት፡፡
ትኩረቱን ቴክኖሎጂ ላይ ያደረገው ይህ ኩባንያ ከሁለት ዓመት በፊት ቻትጅፒቲ የተሰኘ እና ዓለምን ያነጋገረ ቴክኖሎጂ ይፋ አድርጓል፡፡
በሳም አልትማን የሚመራው ቻትጅፒቲ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ካስተዋወቀ በኋላ በመላው ዓለም ትኩረትን ሊስብ ችሏል፡፡
ኦፕንአይ ኩባንያ መጀመሪያ ላይ የተቋቋመው ለትርፍ አለመሆኑን ተከትሎ በዓለም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውድድር ላይ ጉዳት እያደረሰበት ነው ተብሏል፡፡
የኤአይ ቴክኖሎጂ በየጊዜው እየተሻሻለ የመጣ ሲሆን ቻትጅፒቲ ከሌሎች አቻ ውጤቶች ጋር ለመፎካከር የግድ ትርፋማ በሆኑ ስራዎች ላይ መሰማራት እንደሚፈልግ ተገልጿል፡፡
የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሆኑት ኢለን መስክ ኦፕን አይ ኩባንያን ለመግዛት ጥያቄ እንዳቀረቡ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኢለን መስክ እና ሌሎች የንግድ ሰዎች ባንድ ላይ ሆነው ኦፕን አይ ኩባንያን በ97 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ጥያቄ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ተደርጎባቸዋል፡፡
ኦፕን አይ ኩባንያ እንዳስታወቀው ቻትጅፒቲን የበለጠ ለማዘመን እና አሁን ያለበትን የበላይነት ለማስቀጠል የግድ ትርፋማ በሆኑ ስራዎች ላይ መሰማራት አለበት እንጂ ለሽያጭ አይቀርብም ብሏል፡፡