ቻትጂፒቲ ያስተዋወቀው “ጂፒቲኤስ” ምንድን ነው?
“ጂፒቲኤስ” የፕሮግራሚንግ እውቀት የሌላቸው ጭምር የራሳቸውን የቻት እና ምክር ቦት ዲዛይን ማድረግ ያስችላል
የኦፕንኤአይ ኩባንያ ንብረት ቻትጂፒቲ በሳምንት ከ100 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች አሉት
የቻትጂፒቲ ፈጣሪ ኩባንያ ኦፕንኤአይ አዳዲስ አገልግሎቶችን አስተዋውቋል።
የአሜሪካው ኩባንያ ያስተዋወቀው አዲስ አገልግሎት “ጂፒቲኤስ” ይሰኛል።
አገልግሎቱ ምንም አይነት የፕሮግራሚንግ እውቀት የሌላቸው የቻትጂፒቲ ተጠቃሚዎች ጭምር የቻት እና ምክር መጠየቂያ ገጾችን እንደፈለጉት ዲዛይን እንዲያረጉ ያስችላል ተብሏል።
“ጂፒቲኤስ” ህጻናትን ሂሳብ ማስተማር እና የቦርድ ጌም ህጎችን ለማጥናት እንደሚያስችልም ነው የተነገረው።
ኦፕንኤአይ “ላውንደሪ በዲ” የተሰኘ ከልብስ እጥበት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን የሚመልስ መተግበሪያ ማስተዋወቁ ይታወሳል።
“ነጎሼተር” የሚል መጠሪያ ያለው የኦፕንኤአይ አገልግሎትም በክርክር ሂደት ያሉ ጉዳዮች ላይ አሸናፊ የሚያደርጉና ጥቅምን የሚያስከብሩ ምክሮችን ይሰጣል።
ባለፈው አመት ህዳር ወር በተዋወቀ በቀናት ውስጥ ሚሊየን ደንበኞችን ያፈራው ቻትጂፒቲ አሁን በሳምንት ከ100 ሚሊየን ተጠቃሚዎች አሉት።
አዳዲስ ያስተዋወቃቸው አገልግሎቶችም የቻትጂፒን ተደራሽነት ይበልጥ እንደሚጨምርለት የኩባንያው ፕሬዝዳንት ሳም አልትማን።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን የሚጠቀመው ቻትጂፒቲ የማይሰጠው አገልግሎት የለም ማለት ይቻላል።
ቴክኖሎጂው ስራን ከማቅለሉ ባለፈ ግን ሚሊየኖችን በተለይ የቢሮ ሰራተኞችን ከስራ የማሰናበት እድሉ ከፍተኛ ነው መባሉ ስጋት ፈጥሯል።
የፈጠራ ስራን ያለባለቤቱ ፈቃድ የመጠቀሙና የተሳሳቱ መረጃዎችን የማጋራቱ ጉዳይም አከራካሪ ሆኖ ቀጥሏል።
የግዙፍ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ስራ አስፈጻሚዎችም በቅርቡ የሰው ልጅ ህልውናን ይፈትናል ስለተባለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ምክክር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።