በቻትጂፒቲ ሚስቱን የመረጠው ሩሲያዊ
የ23 አመቱ የሶፍትዌር አበልጻጊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቦት በመፍጠር ነው መስፈርቱንን የምታሟላ ውሃ አጣጩን የመረጠው
ወጣቱ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ያፀደቀለትን ምርጫ ተቀብሎ ትዳር መስርቷል
ሩሲያዊው ወጣት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሚስቱን እንዲመርጥ እንዳገዘው ገልጿል።
አሌክሳንደ ዛዳን የተባለው ግለሰብ ቻትጂፒቲ ባለውለታዬ ነው ብሏል።
የ23 አመቱ የሶፍትዌር አበልጻጊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቦት በመፍጠር በቲንደር ላይ የትዳር አጋሩ የምትሆን እንስትን ሲፈልግ ቆይቶ እንደተሳካለት ይገልጻል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቦቱ የትዳር አጋር የሚፈለግበት ቲንደር ላይ 5 ሺህ ከሚሆኑ ሴቶች አንዷን እንዲመርጥለት የተለያዩ መስፈርቶችን ማስገባቱን መናገሩንም የሩሲያው አርኤይኤ ኖቮስቲ ዘግቧል።
“ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቦቱ ቀጣይ ሚስቴን እንዲመርጥልኝ መስፈርቶችን አስገብቻለሁ፤ በመጀመሪያ ከሶፍትዌሩ ጋር ለመግባባት ተቸግሬ ነበር፤ በሂደት ግን እያሰለጠንኩት ሴቶችን እንዴት ማውራት እንዳለብኝ ጭምር ረድቶኛል” ብሏል ዛዳን።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቦቱ ለትዳር የማይሆኑ እንስቶችን ከዝርዝሩ በማስወጣት የተወሰኑትን እንደ ዛዳን በመሆን ሲያወራ መቆየቱም ተገልጿል።
ከየትኞቹ ሴቶች ጋር ማውራት መቀጠል እንዳለበት ከመጠቆም ባለፈ የመጀመሪያ ቀጠሯቸው መምሰል እንዳለበት ሃሳቦችን ሲያጋራ የቆየው ቦት ካትሪና ኢምራኖቭና የተባለች እንስት ጋር እንዲገናኙ መጻጻፉንም ነው የ23 አመቱ የሶፍትዌር አበልጻጊ የተናገረው።
የቻትጂፒቲ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቦቱን “ከካትሪና ጋር የተመጣጠነ እና ጠንካራ ትዳር ይኖራችኋል” ምክረሃሳብ የተቀበለው ዛዳን፥ ካትሪናን በአካል እንዳገኛትም የወደፊት ሚስቱ እንደምትሆን እርግጠኛ መሆኑን ያስታውሳል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቦት ሲያወራት የከረመችው ካትሪና ጉዳዩን ያወቀችው ትዳር ከፈጸሙ በኋላ ነው ተብሏል።
ከምንፈልገው መልክ፣ የኢኮኖሚ ሁኔታ እና ሌሎች መመዘኛዎች አንጻር መስፈርቶችን በማስገባት የምርጫችን እንድናገኝ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከፍተኛ ድርሻ አለው የሚለው የሶፍትዌር ባለሙያ፥ ቴክኖሎጂው ያጸደቀለትን ሚስቱን አግብቶ ጎጆ ቀልሷል።