የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሩሲያ ጦር አዲስ መንደሮችን አልያዘም ሲል አስተባብሏል
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ የሩሲያ ጦር በምስራቅ ዩክሬን ሁለት መንደሮችን መቆጣጠሩን አስታውቋል።
ጦሩ በተከታታይ አዲስ መንደር መቆጣጠሩን ሲያሳውቅ ይህ ሁለተኛው ነው።
ነገርግን የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሩሲያ ጦር አዲስ መንደሮችን አልያዘም ሲል አስተባብሏል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የሩሲያ ጦር በካርኪቭ ግዛት የስቴፖቭ ኖቮስሊቭካ መንደርን እና በዶኔስክ ግዛት ደግሞ ኖቮፖክሮቭስኪ መንደርን ተቆጣጥሯል።
የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ምሽቱን ባወጣው ሪፓርት በካርኪቭ አቅርቢያ በኩፒያንስ የተቃጡ 17 ጥቃቶችን መክቶ መመለሱን ጠቅሷል። ዋና አዛዡ ጦርነቱ በምስራቅ አቅጣጫ በሲንኪቭካ እንደቀጠለ ነው ብለዋል።
ሩሲያ ኃይሎች ባለፈው የካቲት ወር አብዲቪካን ከተማን ከተቅጣጠሩ ወዲህ በርካታ መንደሮችን መቆጣጠር ችለዋል። በምስራቅ እና ደቡብ ዩክሬን 1000 ኪሎሜትር በሚሸፍነው የጦር ግንባር ዶኔስክ እና ካርኪቭ ዋነኛ የትኩረት ቦታ ናቸው።
የሩሲያ ጦር ሁለቱን መንደሮች መቆጣጠሩን ከመግለጹ ከአንድ ቀን በፊት የዩክሬን ጦር በእነዚህ ከተሞች አቅራቢያ የተቃጡ ጥቃቶችን መከላከል መቻሉን ገልጾ ነበር።
የምሽቱ የዩክሬን ጦር አዛዥ መግለጫ በሁለቱም አካባቢዎች ከባድ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል። አዛዡ 44 የሩሲያ ጥቃቶች መመከታቸውን እና 14 የሚሆኑ ግጭቶች እየተካሄዱ እንደሚገኙም አክለው ተናግረዋል።
የዩክሬን ጦር እንደገለጸው ከሆነ ሩሲያ በሰሜናዊ የዩክሬን ድንበሮች ቸርኒቪህ እና ሱሚ ግዛቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኃይል አሰማርታለች። ሩሲያ አዲስ ግንባር ልከተፍት ስለምትችል በእነዚህ አካባቢዎች ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብሏል ጦሩ።
ሩሲያ በፈረንጆቹ የካቲት 22 በዩክሬን ላይ የከፈተችው "ልዩ ወታደራዊ እርምጃ" ሊቆም አልቻለም።
በዩክሬን እያካሄደች ባለው ዘመቻ ከምዕራባውያን የማዕቀብ ናዳ የወረደባት ሩሲያ፣ በከፊል የያዘቻቸውን አራት የዩክሬን ግዛቶች ሙሉ በሙሉ እስከምትቆጣጠር ድረስ ጦርነቱ እንደሚቀጥል መግለጿ ይታወሳል።