የኦሮሚያ ክልል “በርካታ” ንጹሃን ለተገደሉበት ጥቃት ሸኔን ተጠያቂ አደረገ
በአርሲ ዞን ሼካ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት በጥቂቱ የ36 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል
የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻናት ሰራዊት በታንዛኒያ ያደረጉት ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል
የኦሮሚያ ክልል “በርካታ ንጹሃን” ለተገደሉበት ጥቃት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ)ን ተጠያቂ አድርጓል።
በክልሉ አርሲ ዞን ሼካ ወረዳ በሶስት መንደሮች ላይ በተከፈተ ጥቃት በጥቂቱ 36 ሰዎች መገደላቸውን ሬውተርስ ነዋሪዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ ጥቃቱን የፈጸሙት የሸኔ ታጣቂዎች መሆናቸውን ባወጡት መግለጫ ጠቁመዋል።
ሸኔ በወሰደው “ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ብዙ ዜጎች ገድሏል፤፡ ቤት ንብረታቸውንም አቃጥሏል” ያሉት ሃላፊው፥ ቡድኑ የራሱን የመደራደር አቅም ከፍ ለማድረግ ሰላማዊ ዜጎቸ ላይ ያነጣጠረ እርምጃ መውሰዱን እንደገፋበትም አንስተዋል።
መንግስት በወሰደው እርምጃም በምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ቡኖ በደሌን ለማጥቃትና ለማውደም ሲንቀሳቀስ የነበረው የሸኔ ቡድን ሙትና ቁስለኛ ሆኗል ነው ያሉት።
እየተወሰደ ባለው እርምጃ የተደናገጠው የሽብር ቡድኑ በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጥቃቶችን ማድረሱንም የሽብርተኝነቱ ማሳያ አድርገው አቅርበውታል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ስራዊት (ሸኔ) በታንዛኒያ በሁለት ዙር ያደረጉት ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
“የሽብር ቡድኑ ለድርድር ይዞ የቀረበው የጋላቢዎቹን አጀንዳ ነው፤ ይህ የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ ተቀባይነት የለውም” ያሉት የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው፥ ሸኔ ተገዶ ወደ ሰላም እንዲመጣ መንግስት የተቀናጀ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
“የሽብር ቡድኑ ከሽብር ተግባሩ ተቆጥቦ ወደ ሰላማዊ ውይይትና ንግግር ከተመለሰ መንግሥት ለሰላም ሁልጊዜም በሩ ክፍት ነው” ሲሉም ነው አቶ ሃይሉ የተናገሩት።
ሸኔ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ለተነሳው ወቀሳ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሸኔን በሽብርተኝነት መፈረጁ የሚታወስ ነው።