በደራ ወረዳ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ከሌሊት ጀምሮ ጥቃት መክፈታቸውን ነዋሪዎች ገለጹ
ኦነግ ሸኔ በደራ እና አካባቢው ከባድ ጥቃት ሲያደርስ አንድ ዓመት እንዳለፈው ነዋሪዎች ተናግረዋል
የደራ ወረዳ አስተዳዳሪ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ወደ ጉንዶመስቀል ከተማ መግባታቸውን ተናግረዋል
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ከዛሬ ሌሊት ስምንት ሰዓት ጀምሮ በነዋሪዎች ላይ ተኩስ እንደከፈቱ አስተያየታቸወን ለአል ዐይን የሰጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የደራ ወረዳ መዲና በሆነችው ጉንዶ መስቀል ከተማ ነዋሪ የሆኑ እና ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሰዎች ለአል㙀ዐይን እንዳሉት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ዘልቀው በመግባት ከባድ ጥቃት እያደረሱ እንደሆኑ ተናግረዋል።
የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተለይም ከህዳር 2014 ጀምሮ በደራ ወረዳ ስር ባሉት የጉንዶመስቀል ከተማ እና አጎራባች ቀበሌዎች ላይ ታዋቂ ሰዎችን መግደል፣ ማገት፣ መዝረፍ እና ሌሎች ጥቃቶችን እያደረሱ እንደሆነ ነዋሪዎቹ አክለዋል።
ዛሬ ሌሊት በገጠር ቀበሌዎች ላይ የተጀመረው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጥቃት ጨምሮ ዛሬ ማለዳ ሶስት ሰዓት ላይ ወደ ጉንዶመስቀል ከተማ በመግባት ተኩስ በመክፈት የመንግስት እና የግለሰብ ንብረቶችን እየዘረፈ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
በጉንዶመስቀል ከተማ ዙሪያ ባሉ ቀበሌዎች የሚኖሩ ዜጎች መኖሪያ ቤቶች በታጣቂዎቹ እየተቃጠለ እና ከብቶቻቸው እየተወሰዱባቸው እንደሆነም ከቅርብ ዘመዶቻቸው በስልክ መስማታቸውንም ነዋሪዎቹ ነግረውናል።
የሸኔ ታጣቂዎችን ጥቃት የአካባቢው ነዋሪዎች እና ሚሊሻ ለመመከት እየጣሩ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ የመንግስት የጸጥታ መዋቅር በስፍራው ላይ እንደሌሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
እነዚህ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ በገጠር ቀበሌዎች ላይ ጥቃት በመክፈት የቀበሌ አመራሮችን አግተው ወስደው ከቤተሰቦቻቸው ከ400 ሺህ በላይ ብር ቢቀበሉም አመራሮቹ እስካሁን ወደ ቤታቸው እንዳልተመለሱም ከነዋሪዎቹ ሰምተናል።
የታጋች ቤተሰቦችም ከኦነግ ሸኔ የተጠየቁትን ገንዘብ ከሰጡ በኋላ አለመለቀቃቸውን ተከትሎ መገደላቸውን በማመን ውሎ ማዋላቸው ተገልጿል።
የደራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ውብሸት አበራ በበኩላቸው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ወደ ጉንዶመስቀል ከተማ መግባታቸውን ለአልዓይን ተናግረዋል።
“ታጣቂዎቹ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በከተማዋ ባሉ ባንኮች፣ የመንግስት ተቋማት እና የግለሰቦችን ንብረት እየዘረፉ ነው” ያሉት አስተዳዳሪው የክልል እና የፌደራል የጸጥታ ሀይል እንዲገባላቸው ማመልከታቸውንም ገልጸዋል።