በመንግስትና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) መካከል ሲደረግ የነበረው ንግግር ያለስምምነት ተጠናቀቀ
በሁለት ዙር ሲካሄድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን መንግስት አስታውቋል
መንግስትና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) በታንዛኒያ የሰላም ንግግር በማድረግ ላይ ነበሩ
በመንግስትና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) መካከል ሲደረግ የነበረው ንግግር ያለስምምነት መጠናቀቁ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና መንግሥት "ሸኔ" ብሎ በአሸባሪነት የፈረጀውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ድርድር ሲካሄድ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን በኤክስ ገጻው ባወጡት መረጃ፤ ለሁለተኛ ጊዜ በታንዛኒያ ሲካሄድ የነበረው ንግግር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የፌደራል መንግስት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ሳቢያ እየደረሰ ያለውን ስቃይ ለማስቆም ካለው ፍላጎት ሳቢያ ከሸኔ/ኦነግ ጋር የሰላም ድርድር ሲያደርግ መቆየቱን እና የሁለቱም ዙር ድርድር ያለስምምንት መጠናቀቁን ነው አምባሳደር ሬድዋን ያስታወቁት።
መንግስት በነገሮች ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረብ ቢያደርግም ሳይሳካ መቅረቱንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) መካከል ሁለተኛ ዙር ንግግር በታንዛኒያዋ ዳሬሰላም ለሳምንታት ሲካሄድ መቆይቱ ይታወቃል።
መንግሥት "ሸኔ" ብሎ በአሸባሪነት የፈረጀውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ፤ በቡድኑ መሪ ጃል መሮ (ድሪባ ኩምሳ) እና በምክትላቸው ጃል ገመቹ አቦየ ከፍተኛ አመራሮቹ በታንዛኒያ ከፌደራል መንግስት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን አስታውቆ ነበር።
በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና በኦነግ ሸኔ መካከል ከወራት በፊት በታንዛኒያ ከፊል ራስ ገዟ ዛንዚባር ለድርድር ተተቀምጠው ንደነበረ እና ድርድሩ ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2013 ግንቦት ወር ላይ በኦሮሚያ ክልል ታጥቆ የሚንቀሳቀሰውን "ኦነግ ሸኔ" ቡድን በሽብርተኝትነት መፈረጁ የሚታወስ ነው።