የጨፌ ኦሮሚያ አባልና የነቀምቴ ከተማ የቀድሞ ከንቲባን ያለ መከሰስ መብት አንስቷል
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ወይም ጨፌ ኦሮሚያ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ጉባኤ ዛሬ አጠናቋል፡፡
ምክር ቤቱ በመጨረሻም የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን ላለፉት ዓመታት የክልሉን ፖሊስ በኮሚሽነርነት ሲመሩ ለቆዩት አራርሳ መርዳሳ አዲስ ሀላፊነት ሰጥቷል፡፡
አቶ አራርሳ የኦሮሚያ ክልል አስተዳድር እና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ ሆነው ሲሾሙ በተጨማሪም ምክር ቤቱ የነቀምቴ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ እና የምክር ቤቱ አባል የሆኑት የአቶ ቶሌራ ረጋሳ ጨዋቃን ያለ መከሰስ መብታቸውን አንስቷል፡፡
የቀድሞ ከንቲባው ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የቀድሞ የከተማው የብልጽግና ሃላፊ የነበሩት አቶበደሳለኝ ቦኮንጃ ግድያ ወንጀል ተጠርጥረው ነው ተብሏል፡፡
ጨፌ ኦሮሚያ የክልሉን የ2016 ዓ.ም በጀት የቀረበውን 221 ቢሊየን 517 ሚሊየን 956 ሺህ 655 ብር በጀት በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡
ከጸደቀው በጀት ውስጥ ለወረዳ እና ለከተሞች ወጪ 137 ነጥብ 8 ቢሊየን፣ ለክልሉ ወጪ 83 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር፣ ለክልሉ ካፒታል ወጪ 54 ነጥብ 25 ቢሊየን ብር እንዲሁም ለመጠባበቂያ 600 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቧል፡፡
በተጨማሪም ጨፌ ኦሮሚያ በጉባዔው ለ2015 በጀት አመት የቀረበውን ተጨማሪ 13 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በጀት አፅድቋል፡፡
በሌላ በኩል ጨፌው የ53 ዳኞችን ሹመት አጽድቋል።