ባለፈው አንድ ወር 370 የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መደምሰሳቸው ተገለጸ
የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ ኦነግ ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው የክልሉ አካባቢዎች እርምጃ በመውሰድ ላይ ነው
ከተደመሰሱት በተጨማሪ 331 የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እና በርካታ የጦር መሳሪያዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል
የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ የህወሃት ጁንታ ተላላኪ በሆነው ኦነግ ሸኔ ላይ ሲወስድ በነበረዉ እርምጃ 370 መደምሰሳቸው ተገልጿል፡፡ 176 ታጣቂዎች ደግሞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውሉ 154 ደግሞ በህዝቡ ተይዘዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ትጥቅና ስንቅ ለሽፍታዉ ሲያቀርቡ የነበሩ 183 የሕወሓት አባላትም በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡
በሎጂስቲክ በኩል 4 ብሬኖችን ጨምሮ 1,585 ጠመንጃዎች፣ 10,902 ጥይቶች፣ 605 ከብቶች፣ 353 ፍየሎች፣ 54 አህዮች፣ 48 ግመሎች፣ 682,680 ብር እና 204,000 ሀሰተኛ ገንዘብ መያዙንም ፓርቲው አስታውቋል፡፡
በትግራይ ክልል የፌዴራል መንግስት የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተከትሎ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችም ላይ የተጠናከረ እርምጃ ሲወሰድ መቆየቱን መንግስት አስታውቋል፡፡
በተለይም ኦነግ ሸኔ በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው በምዕራብ ፣ በምስራቅ እና በደቡብ የኦሮሚያ አካባቢዎች ባለፈው አንድ ወር የኦሮሚያ ፖሊስ ተልዕኮ ተሰጥቶት እርምጃ ሲወስድ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ በሕወሓት በተፈጸመው ጥቃት የኦነግ ሸኔ ወታደሮችም መሳተፋቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡