የህወሓት እና ሸኔ በአሸባሪነት መሰየም “የሽብር ተግባሩን ለማስቆም እና ዐቅማቸውን ለማዳከም ያስችላል”- ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
ንብረቶቻቸውን በመውረስ የፋይናንስ አቅማቸውን ለማዳከም እንደሚያግዝም ባወጣው መግለጫው አስታውቋል
ውሳኔው ሰላማዊ ዜጎች ከድርጅቶቹ ጋር እንዳይተባበሩ ለማድረግ ያግዛልም ነው ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያለው
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና “ሸኔ”ን በአሸባሪነት መሰየማቸውን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫው በአሸባሪነት ለመሰየም ያበቋቸውን ምክንያቶች በዝርዝር አብራርቷል፡፡
ባለፉት 3 አመታት ከበስተጀርባ የፖለቲካ አስተሳሰብን መነሻ በማድረግ እና የፖለቲካ አላማን ወይም ግብን ለማሳካት በማሰብ ሲፈጸሙ በነበሩ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ሞተዋል፣ተፈናቅለዋል ንብረት ወድሟልም ያለው ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ህወሓት መንግስትን ከስልጣን ለማስወገድ በማሰብ ከፍተኛ ወታደራዊ ስልጠና ይሰጥና ህዝቡንም ለጦርነት ያዘጋጅ እንደነበር አስታውቋል፡፡
በክልሉ ይገኝ የነበረው የሃገር መከላከያ ሰራዊት በሚፈለገው ልክ መንቀሳቀስ እንዳይችል በየቦታዉ ኬላዎችን በማቋቋም ፍተሻዎችን ያደርግም እንደነበርም ነው የገለጸው፡፡
በሌሎች የሃገሪቱ ክልሎች እና አካባቢዎች ችግርለመፍጠር በማሰብ የበጀት እና የጦር መሳርያ ድጋፍ ሲያደርግ ነበርም ብሏል፡፡
ከነዚህ ህወሓት ሲደግፋቸው ከነበሩ ቡድኖች መካከል በተለምዶ “ሸኔ” ተብሎ የሚጠራውና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰዉ ቡድን አንዱ ነው፡፡
ቡድኑ የበርካቶችን ህይወት እንዲያጠፋ፣ እንዲያፈናቅል እና ንብረት እንዲያወድም ከማገዝ ባለፈ ታጣቂዎቹን በአጋዥነት አሰልፎ በጋራ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ማጥቃቱንም ነው ያስታወቀው፡፡
“ሸኔ” በ2013 ዓ.ም ብቻ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ 463 ሰዎች ላይ አደጋ አድርሷል፡፡
በጥቅምት 22ቱ የምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንካ ቀበሌ የንጹሃን ጥቃት 36 ንፁሃን ዜጎችን የገደለም ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለዉን ሰዉ አፈናቅሏል በርካታ ቤቶችንም አቃጥሏል፡፡
አባ ቶርቤ የተባለ ገዳይ ቡድን በማዋቀር ይንቀሳቀሳልም ነው ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያለው፡፡
በዚሁ መሰረት ቡድኖቹ “አሸባሪ ድርጅት ወይም ቡድን” ተብለው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰየማቸውንም ነው የገለጸው፡፡
ይህ መሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ከድርጅቱ ጋር እንዳይተባበሩ ለድርጅቱም ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ ይጠቅማል ብሏል።
በህብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን የሽብር ተግባር የማስቆም እና ህግ አስከባሪ አካላት ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተጨማሪ አቅም እንዲፈጥሩ የማስቻል አላማ እንዳለውም አስታውቋል፡፡
ሰዎች እንዳይተባበሩ በማድረግ የሰው ሃይል ተሳትፎውን ለመቀነስ ንብረቶቹን በመውረስ የፋይናንስ አቅሙን ለማዳከም ያግዛል ሲልም ነው መግለጫው የሚያትተው፡፡
ቡድኖቹን በሽብርተኝነት የመፈረጁ ውጥን ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የመጣ ነው፡፡
ምክር ቤቱ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በቀረበለት በዚህ ጉዳይ ላይ ከተወያየ እና ሃሳቡን ከደገፈው በኋላ ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል፡፡
ባሳለፍነው ሃሙስ በቀረበለት የውሳኔ ሃሳብ ላይ የመከረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንድ የተዓቅቦ ድምጽ በአብላጫ ቡድኖቹ ሽብርተኛ ሆነው እንዲሰየሙ ሲል መወሰኑ ይታወሳል፡፡