በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ ለተፈጸመው “አሰቃቂ ግድያ” የክልሉ መንግስት “ፋኖ” እና “ሸኔ”ን ተጠያቂ አደረገ
የኦሮሚያ ክልል መንግስት “የፋኖ ታጣቂዎች ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ሲፈጽሙ ሸኔ ትጥቅ በማስፈታት ሁኔታዎች አመቻችቷል” ብሏል
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ግድያውን ያወገዘ ሲሆን፤ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በአንድ ወጣት ላይ አሰቃቂ ግድያ ሲፈጸም የሚያሳይ ምስል መውጣቱን ተከትሎ ቁጣ ቀስቅሷል።
በያዝው ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት ላይ የደራ ወረዳ ነዋሪ የሆነ ወጣት ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ሲገደል የሚያሳይ ምስል በማህራዊ ትስስር ገጾች ላይ መለቀቁን ተከትሎ ጉዳዩ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን፤ በርካቶች ቁጣቸውን በማሰማት ላይ የገኛሉ።
ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ከአካባቢው ነዋሪዎች አገኘው ባለው መረጃው ግድያው የተፈጸመው ከሁለት ወራት በፊት መሆኑን እና ግድያው የተፈጸመበት ወጣት ደረጀ አማረ ተስፋ እንደሚባል አስታውቋል።
ግድያው የተፈጸመው በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ “የፋኖ ታጣቂዎች” መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ ብሏል በዘገባው። ነገር ግን ይህንን ክስ በተመለከተ ከፋኖ ቡድን የተሰጠ ምላሽ የለም።
የግድያው ምስል መለቀቁን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የከፍተኛ ትምህር ተቋማት በዛሬው እለት ግድያውን የሚያወግዙ ሰላማዊ ሰልፎች መካሄዳቸውም ተሰምቷል።
ስለፈኞቹ ኦሮሚያ ክልል እየተፈፀሙ ያሉትን ጭካኔ የተሞላ ግድያዎች አንዲቆሙ የጠየቁ ሲሆን፤ የኦሮሚያ ክልል መንግስት የዜጎችን ደህንነት እንዲጠብቅም ጠይቀዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ “ጽንፈኛ ኃይሎች” ብሎ በጠራቸው አካላት የተፈጸመውን ጭካኔ የተሞላበት ግድያ እንደሚያወግዝና የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሚሰራ አስታውቋል።
የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ለመገናኛ ብዙሃ በሰጡት መግለጫ፤ “በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የተፈጸመው ግድያ ‘የፋኖ ጽንፈኛ ኃይሎች’ ለህዝቡ እና ለብሄር ብሄረሰቦች ያላቸውን ጥላቻ ያሳየ ነው” ብለዋል።
“የፋኖ ጽንፈኛ ኃይሎች” እና “የሸኔ ታጣቂዎች” ጭካኔ በተሞላበት መልኩ እየፈጸሙ ያሉት ተግባር የብሄር ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ ህዝቡ እንዲጨራረስ ያለመ ነው ብለዋል አቶ ኃይሉ በመግለጫቸው።
“የፋኖ ታጣቂዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ሲፈጽሙ ሸኔ ትጥቅ በማስፈታት ሁኔታዎች አመቻችቷል” ሲሉም አቶ ኃይሉ ተናግረዋል።
“ሸኔም ይሁን ፋኖ ቡድኖቹ የተለያየ ቋንቋ ቢናገሩም የተኛውን ህዝብ አይወክሉም ያሉት ኃላፊው፤ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አግልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) በማበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ “ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሰላሌ -ደራ አካባቢ ጽንፈኛው ቡድን የፈፀመው የአረመኔነት ተግበር ከሰው ልጅ የማይጠበቅ እና መወገዝ አለበት” ብለዋል።
“ሰሞኑን በሰላሌ ደራ ላይ የተፈፀመው አጅግ ሊወገዝ የሚገባው አይነት ሰውኛ ያልሆኑ ድርጊቶች በመፈጸም አማራና ኦሮሞን ለመጨረስ ያልተሞከረበት ጊዜ የለም። ግን ሁሉም አልተሳኩም ብቻ ሳይሆን በዚህ አይነት ኢሞራላዊ ሁኔታ መቼም ቢሆን አይሳካም” ሲሉም ገልጸዋል።
“በእንዲህ አይነት እኩይ ድርጊት የተሰማሩትን አረመኔዎች መላው ህዝብ እና መንግስት በተባበረ ክንድ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው ስርዓት እንዲይዙ ያደርጋሉ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሁሉም ይስተካከላል። እየነፈሰ ያለው ሰላምም ይፀናል” ብለዋል።