“ኢትዮጵያ በርካታ ወረራዎችን ስትቋቋም በጥንቃቄ ይዛ የኖረችው ቅርሶቿን ነው” - ፕሬዝዳንት ሣሕለ ወርቅ
መንግስት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ዕድሳት እየተከታተለ መሆኑንም ነው የገለጹት
በኢትዮጵያ መከሰት የሌለበት ችግር ማጋጠሙን ያነሱት ሣህለ ወርቅ የላሊበላ ሕዝብ ሰላም እንጂ የባለፈው አይነት ችግር አይገባውም ብለዋል
የኢትዮጵያ መንግስት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ዕድሳት እየተከታተለ መሆኑን ፕሬዝዳንት ሣሕለ ወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ለገና በዓል ላሊበላ የተገኙት ፕሬዝዳንቷ “ይህ ድንቅ ቦታ” ከፈረንሳይ መንግስት በተገኘ ዕርዳታ ይታደሳል ብለዋል፤ ለሕዝብ ባደረጉት ንግግር፡፡
በዚህም ላሊበላ የበለጠ ቱሪስት እንደሚስብ የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ሣሕለ ወርቅ መንግስት ይህንን ሁኔታ በቅርብ እየተከታተለው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሣሕለ “ኢትዮጵያ በርካታ ወረራዎችን ስትቋቋም በጥንቃቄ ይዛ የኖረችው ቅርሶቿን ነው” እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን ይህንን ቅርስ በቤተሰብ ደረጃ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደሚሸጋገር ውድ እንቁ ተጠንቅቆ መጠበቅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ያለፉት ትውልዶች የላሊበላን ዓለም አቀፍ ቅርስ ከየትኛውም ጥቃት ከጥቃትና ከተፈጥሮ አደጋ ሲከላከሉት እንደቆዩ ገልጸዋል፡፡
ላሊበላ ባለፉት ወራት በወረራ ላይ እንደነበረች የተናገሩት ፕሬዝዳንቷ፤ ነዋሪዎችም የመዘረፍና የመደፈር አደጋ ሲደርስበት እንደነበር አንስተዋል፡፡ የዚህ ታሪክ ተረካቢ ሕዝብ በሰላም እንዲኖርእንጅ ባለፉት ወራት ያየነውን አይነት ችግር እንደማይገባውም ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቷ ላሊበላ የተገኙት ሕዝቡን “አይዟችሁ” ለማለት እንደሆነ ገልጸው፤ ላሊበላ የዓለም ቅርስ በመሆኑ የዓለም ቱሪስቶች እንዲመጡ ለማድረግ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ ላሊበላ ከፍተኛ ተስፋ ያላት ከተማ መሆኗን የገለጹት ፕ/ት ሣሕለ ከተማዋን ወደነበረችበት ቦታ መመለስ ሳይሆን ከዚያም ማስበለጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ከፈረንሳይ መንግስት በተገኘ ዕርዳታም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲናት ዕድሳት እንደሚደረግላቸውም ፕሬዝዳንቷ አረጋግጠዋል፡፡
ይህም የበለጠ ቱሪስት እንደሚስብም ያነሱ ሲሆን፤ መንግስት ይህንን ሁኔታ በቅርብ እየተከታተለው ስለመሆኑ አረጋግጠዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ገናን በላሊበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ መውሊድና አረፋን በነጃሺ፣ ጽዮን ማርያምን በአክሱም፣ እሬቻን በቢሾፍቱ፣ ጨምበላላን በሃዋሳ ሌላውን ደግሞ በጅግጅጋ፣ በጋምቤላ፣ በሰመራ፣ በሃረር፣ በሌሎቹ ሁሉ የሀገሪቱ ከተሞች በመተባበር “ስናከብር ያምርብናል” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተከሰተው መሆንና መከሰት የሌለበት እንደሆነ የተናገሩት ሣሕለ ወርቅ ፤ ይህ እንዳይደገም “ሁሉም አይሆንም” ማለት አለበት ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቷ፤ ኢትዮጵያውያን “የሃሳብ ልዕልናን ከተቀበልን የመፋለሚያ ቦታው በጠረጴዛ ዙሪያ እንጂ ጦር በመማዘዝ እንዳይሆን” ማድረግ ይገባናል ብለዋል፤ ችግሮችን ለጊዜያዊ ፋታ ብቻ ሸፍኖ ማለፍ ሳይሆን ስር መሰረቱን አውቆ መፍትሄ በመፈለግ ፤ ስህተትን በመቀበልና በመታረም ማስተካከል እንደሚገባ በመጠቆም፡፡