ሩሲያ እና ቻይና በጋራ ድሮን ማምረት መጀመራቸው ተነገረ
ሞስኮ የባለስቲክ ሚሳኤል፣ ታንክ፣ አውሮፕላን እና ሌሎች ግብአቶችን ከቤጂንግ በስፋት ማስገባቷንም አሜሪካ ገልጻለች
ሩሲያን ከምዕራባውያን ማዕቀብ እየታደገች በምትገኘው ቻይና ላይ የአውሮፓ ሀገራት ማዕቀብ እንዲጥሉ እየተጠየቀ ነው
ሩሲያ ከሶስት አስር አመት ወዲህ ግዙፍ ወታደራዊ አቅም እንድትገነባ ቻይና እያገዘቻት ነው አለች አሜሪካ።
የዋሽንግተን የስለላ ተቋማት ደርሰውበታል የተባለውን መረጃ ስማቸው ያልተጠቀሰ የባይደን አስተዳደር ባለስልጣናት ይፋ ማድረጋቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
የስለላ መረጃው ቻይና ለሩሲያ የሚሳኤል ፕሮግራም፣ ለታንኮች፣ አውሮፕላኖች እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች መስሪያነት የሚውሉ ግብአቶችን በስፋት እየላከች ነው።
ሞስኮ በ2023 ካስገባችው ለሚሳኤል መስሪያነት የሚውል ግብአት (ማይክሮኤሌክትሮኒክስ) 90 በመቶው ከቤንጂንግ የተላከ ነው ተብሏል።
የቭላድሚር ፑቲን ሀገር ባለፈው አመት የመጨረሻ ሩብ አመት ብቻ ከቻይና 900 ሚሊየን የሚያወጡ የተለያዩ ማሽኖችን ማስገባቷንም ነው የጠቆመው መረጃው።
ሁለቱ ሀገራት በሩሲያ በጋራ ድሮን በመስራት ላይ መሆናቸውም ቻይና በዩክሬኑ ጦርነት እጇን እያስገባች እንደምትገኝ ያመላክታል በሚል አሜሪካ ማዕቀብ እንድትጥልባት ጠይቋል።
የአሜሪካ የስለላ መረጃ በዚህ ሳምንት ወደ ቤጂንግ የሚያቀኑት የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ ከቻይና ባለስልጣናት ጋር ሲመክሩ ጉዳዩን አጽንኦት እንዲሰጡት ያደርጋልም ተብሏል።
የቡድን ሰባት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቀጣዩ ሳምንት በጣሊያን የሚካሂዱት ምክክር ላይም አጀንዳቸው ይሆናል መባሉን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ማዕቀብ የተጣለባት ሩሲያ ከቻይና ጋር ሁለንተናዊ ወዳጅነቷን በማጠናከር ፈተናዎችን ለመሻገር እየሞከረች ነው።
የአሜሪካ የስለላ መረጃም ከሶቪየት ህብረት ዘመን ወዲህ ከፍተኛ ወታደራዊ መስፋፋት ላይ እንደምትገኝ አመላክቷል።
ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለስልጣን “አሁን ያለን አማራጭ ዩክሬን እንድታሸንፍ ማድረግና ቻይናን ለሩሲያ ድጋፍ እንዳታደርግ ማሳመን ብቻ ነው” ማለታቸውም ተዘግቧል።
ከአሜሪካ የሚቀርቡ ወቀሳዎችን ስታታጥል የቆየችው ቻይና፥ በቀጥታ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ግብአቶችን መላክና ድሮን በጋራ መስራትን መርጣለች ተብሏል።
የባይደን አስተዳደር የአውሮፓ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ እድገቷ በኮሮና እና ማዕቀብ ምክንያት ያዘገመባት ቤጂንግን እንዲያሳምኑ አልያም በማዕቀብ ጫና አቋሟን እንድታስተካክል እንዲያደርጉ ማሳሰቡ ተገልጿል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቀጣይ ሳምንታት ወደ ቤጂንግ ያቀናሉ።
የሩሲያ አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ባለፈው ማክሰኞ በቤጂንግ ከፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ነው።