በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተነሱት አብደላ ሀምዶክ ለድርድር ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ
የአሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ኖርዌይ አምባሳደሮች ከአብደላ ሀምዶክ ጋር ተወያይተዋል
አብደላ ሀምዶክ ወደ ድርድር ከመገባቱ በፊት ሲቪል አስተዳድሩ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ጠይቀዋል
በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ለድርድር ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ፡፡
በሱዳን ከ10 ቀናት በፊት በሲቪል አስተዳድሩ ላይ መፈንቅለ መንግስት ተፈጽሞ የሱዳን ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አልቡርሀን ሙሉ ለሙሉ ስልጣን መቆጣጠራቸው ይታወሳል፡፡
በርካታ አገራት እና የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት በሱዳን የተፈጸመውን መፈንቅለ መንግስት አውግዘው ስልጣን ለሲቪል አስተዳድሩ እንዲመልስ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ተመድን ጨምሮም በርካታ አገራት ወታደራዊ አመራሩ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድር እንዲመልስ ድርድር እንዲጀመር እየወተወቱ ነው፡፡በሱዳን የአሜሪካ እንግሊዝ እና ኖርዌይ አምባሳደሮች በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ተነስተው በቁም እስር ላይ ከሆኑት አብደላ ሀምዶክ ጋር ተወያይተዋል
የአምባሳደሮቹ ውይይት ዓላማ ሲቪል አስተዳድሩ ስልጣን ከተቆጣጠረው የሱዳን ጦር ጋር በድርድር ስልጣን እንዲጋራ ማመቻቸት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይሁንና አብደላ ሀምዶክ ድርድር ከመጀመሩ በፊት በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተነሳው ሲቪል አስተዳድሩ ወደ ቀድሞ ስራው እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት በበኩሉ በሱዳን የተፈጠረው የፖለቲካ ውጥረት እንዲረግብ ድርድሮች እንዲጀምሩ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡
በሱዳን ያለውን ውጥረት ለማርገብ የፖለቲካ ፓረቲዎች፤አማጺ ቡድኖች፤ከመፈንቅለ መንግስቱ በፊት የነበረው መንግስታዊ መዋቅር እንዲደራደሩ እና የፓርላማ መቀመጫዎች እንዲኖራቸው የሚያስችል የድርድር እቅድ በተመድ በኩል ቀርቧል፡፡
የሱዳን ወታደራዊ አመራር ደግሞ የጸጥታ እና ደህንነት ምክር ቤትን እንዲመራ ማድርግ የሚለው ሌላኛው የተመድ የድርድር ሀሳብ ነውም ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክና የሲቪል መንግስቱ ባለስልጣናትን ከስልጣን ያነሱት የሱዳን ጦር አዛዥ አል ቡርሃን በሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ ባለፈም፤ አል ቡርሃን በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ህብረት እና በፈረንሳይ የሚገኙትን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት የሚገኙ የሱዳን አምባሳደሮችን ከስራ ማባረራቸው አይዘነጋም፡፡
ዲፕሎማቶቹ የሱዳን የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አብደላ ሃምዶክን በመደገፋቸው ከኃላፊነት መነሳታቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡