አብደላህ ሀምዶክን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመመለስ ከስምምነት መደረሱ ተሰማ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ አዲስ ካቢኔ እንዲያዋቅሩም ከስምምነት ተደርሷል
በሱዳን እየተካሄደ ባለው ድርድር ለይ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር ለመልቀቅ ተስማምተዋል
የሱዳን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ኃይሎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክን ወደ ኃላፊነት ለመመለስ ከስምምነት መድረሳቸው ተነግሯል።
የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ሀገሪቱን ከቀውስ ለማውጣት እያካሄዱት ባለው ድርድር ላይ በወታደራዊ ኃይሎች ከስልጣናቸው ተነስተው የነበሩትን አብደላ ሀምዶክ ወደ ቀድሞ ኃላፊነታቸው ለመመለስ ከስምምነት ደርሰዋል።
የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክም በጉዳዩ ላይ ከመግባባት መድረሳቸው ነው የተነገረው።
በድርዱሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የኡማ ፓርቲ መሪ ፋድለላህ ባርማ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናሩት፤ በስምምነቱ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ ካቢኔያቸውን እንዲያዋቅሩ ከስምምነት ተደርሷል።
በተጨማሪም ሁሉም የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር እንዲለቀቁ ከስምምነት መደረሱንም አስታውቀዋል።
።ስምምነት ከተፈረመ በኋላም የሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች አብደላህ ሀምዶክን ወደ ጠቅላይ ሚኒስተርነታቸው የሚመልሱ መሆኑንም ፋድላላህ ባርማ አክለው ተናግረዋል
በተጨማሪም ተደራዳሪ ኃይሎቹ የሱዳንን ግዛታዊ አንድነት ማስጠበቅ፣ የሽግግር ጊዜውን የሚመራውን ሕገ መንግሥታዊ ፣ህጋዊ እና ፖለቲካዊ አስራሮች ላይ ለመወሰን እና ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ተስማምተዋል።
የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ሀገሪቱን ከቀውስ ለማውጣት ባካሄዱት ድርድር እና በደረሱባቸው ስምምነቶች ዙሪያ ዛሬ በይፋ እንደሚፈራረሙም ተነግሯል።
ብዙዎች “መፈንቅለ መንግስት ነው” ባሉት እርምጃ የሱዳን ጦር ባሳለፍነው ወር የሀገሪቱን የሽግግር መንግስት የሚመሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ ሲቪል ባለስልጣናትንና ከፍተኛ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል።
በሱዳን በሃገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን የሚመራ አዲስ ወታደራዊ መንግስት መመስረቱ የሚታወስ ነው።
ይህንን ተከትሎም በወታደሩ ተግባር የተበሳጩ ሱዳናውያን በካርቱም እና በሌሎችም የሀገሪቱ ጎዳናዎች ላይ በመውጣት ቁጣቸውን ሲገልጹ ነበረ ሲሆን፤ በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ በሱዳን ጦር የተገደሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ቁጥር 40 ደርሷል።
ተመድን ጨምሮም በርካታ ሀገራት ወታደራዊ አመራሩ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድር እንዲመልስ ድርድር እንዲጀመር ሲወተውቱ መቆየታቸውም አይዘነጋም።