የሱዳን ጦር፤ ትናንት ከቡርሃን የመከሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ለምን አሰረ?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት እስር ላይ ይገኛሉ
ሆኖም ሃምዶክ የሚመሩትን የሲቪል መንግስት እንዲበትኑ በሌ/ጄ አል ቡርሃን የቀረበላቸውን ጥያቄ አልተቀበሉም
ሱዳን ዛሬ በከፍተኛ የጸጥታ እና ደህንነት ችግር ውስጥ ትገኛለች፡፡ የሃገሪቱ ወታደራዊ አካል የሲቪል ባለስልጣናትን ማልዶ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተከትሎ ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጣ ተቀስቅሷል፤ የኢንተርኔትና ሌሎች የስልክ ግንኙነቶች ተቋርጠዋል፡፡
የምድርም ሆነ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የለም፡፡ ጦሩ ወደ ሱዳን የሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች መግባቱን ተከትሎ ጣቢያዎቹ ስርጭት ማቆማቸውን በካርቱም የአል ዐይን ኒውስ ዘጋቢ ገልጿል፡፡
ጣቢያዎቹ ስርጭታቸውን ያቆሙት እና ሰራተኞቻቸው የተያዙት ጦሩ ሲቪል የሃገሪቱ ባለስልጣናትን ማሰር መጀመሩን ተከትሎ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን የቁም እስረኛ ያደረገው ወታደራዊው አካል በሉዓላዊው የሽግግር ምክር ቤት አባል የሆኑ ሲቪል ሰዎችን ጨምሮ ሚኒስትሮችን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን፣ እንዲሁም የክልል መሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡
ሃምዶክ ለምን በቁጥጥር ስር ዋሉ?
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ሲቪሊያን የሃገሪቱ መንግስት ባለስልጣናት ከሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ወታደራዊ መሪዎች ጋር እስከ ትናንት እሁድ ጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ/ም ምሽት ድረስ ውይይት ላይ ነበሩ፡፡
ውይይቱ አሜሪካ ትናንትና እና ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በካርቱም በጉብኝት ላይ በነበሩት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋ ጄፍሪ ፌልት ማን በኩል ባቀረበችው የመፍትሔ ሃሳብ ላይ ያተኮረ ነበረ፡፡
“በቁም እስር ላይ ናቸው” የተባሉት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደማይታወቅ ቦታ መወሰዳቸው እየተነገረ ነው
አሜሪካ የሚኒስትሮች ምክር ቤቱን እና ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱን እንደገና ማደራጀት (ሪፎርም) ያስፈልጋል ስትል ነበር ሃሳብ ያቀረበችው፡፡
ወታደራዊ አመራሩ ስልጣን እንዲለቅና የሲቪል መንግስት እንዲቋቋም፤ የፍትህ እና ሌሎች ኮሚሽኖች እስከ ቀጣዩ የፈረንጆቹ ወር አጋማሽ ድረስ እንዲቋቋሙም ጠይቃለች፡፡
ፌልትማን በተደረሰው ስምምነት መሰረት አል ቡርሃን በመጪው ሃምሌ ከሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንትነት ወርደው ምክር ቤቱ በሲቪሊያን እንዲመራም አሳስበዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ መሪ ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በመፍትሔ ሃሳቡ ላይ ያላቸውን አቋም እስያዝነው የፈረንጆቹ ጥቅምት ወር መጨረሻ (በ5 ቀናት ውስጥ) ድረስ እንዲያሳውቋቸው ጠይቀዋል፡፡
“የጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ መታሰር አደገኛ ነው”- መሬም አል ሳዲቅ፣ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ሆኖም ሃምዶክ የሚመሩትን የሲቪል መንግስት እንዲበትኑ በሌ/ጄ አል ቡርሃን የቀረበላቸውን ጥያቄ አልተቀበሉም፡፡
ይህን ተከትሎ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ሲቪል ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በጦሩ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የስልክና ሌሎች ኢንተርኔትን መሰል የግንኙነት መንገዶች የዘጋው ጦሩ እንቅስቃሴዎችን ከማገድም በዘለለ የሃገሪቱን የሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስርጭት አስቁሟል፡፡
ከደቂቃዎች በፊት በሰጡት መግለጫ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ያስታወቁት የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ሊቀመንበር ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ምክር ቤቱ መፍረሱን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡