ልዩልዩ
ከሊቢያ ድንበር የተነሱ 100 ስደተኞች በሜድትራኒያን ባህር ውስጥ ሰጥመው ህይወታቸው አለፈ
ሊቢያ ህገ ወጥ ስደተኞች ሜድትራኒያን በህርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመድረስ ለሚያደርጉት ጉዞ ተመራጭ ስፍራ ነች
በፈረንጆች በ2020 በአጠቃላይ 381 ስደተኞች በሜድትራኒያን ባህር ውስጥ ሰጥመው ህይወታቸው አልፏል
መነሻቸውን የሊቢያ የባህር ጠረፍ ያደረጉ ስደተኞችን አሳፍራ የነበረች መርከብ በመገልበጧ ከ100 በላይ ስደተኞች ህይወት ማለፉን ዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ።
የዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) የስራ ኃላፊ ኤጉዊኖ አምብሮሲ በትዊተር ገጻቸው “በዛሬው እለት በሜድትራኒያን ባህር ላይ ቢያንስ የ100 ስደተኞች ህይወት አልፏል” ብለዋል።
ይህም ዓለም አቀፍ ህጎችን እና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር ያልቻሉ ፖሊሲዎች ያስከተሉት የሰብዓዊ ቀውስ ውጤት ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
ሊቢያ በአሁኑ ጊዜ ህገ ወጥ ስደተኞች ሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመድረስ ለሚያደርጉት ጉዞ ተመራጭ ስፍራ ሆናለች።
በፈረንጆች በ2020 በሜድትራኒያን ባህር ላይ ለአደጋ ተጋልጠው የነበሩ 11 ሺህ 891 ስደተኞችን በመታደግ ወደ ሊቢያ እንዲመለሱ መደረጉን የዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) ሪፖርት ያመለክታል።
በዚያኑ ዓመት በአጠቃላይ 381 ስደተኞች ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ 597 ስደተኞች ደግሞ የደረሱበት እንደማይታወቅ ነው የድርጅቱ ሪፖርት የሚያመለክተው።