በብሪታንያ 130 ሺህ ሰዎች አሁንም በዘመናዊ ባርነት ውስጥ ይኖራሉ ተባለ
በሀገሪቱ አሁንም ተገደው በጉልበት ስራ፣ አደንዛዥ እጽ እና በወሲብ ንግድ ውስጥ ያሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተገልጿል

በባርነት ውስጥ ካሉ ዜጎች መካከልም የብሪታንያ፣ አልባኒያ፣ ቬትናም እና ሌሎችም ሀገራት አሉ ተብሏል
በብሪታንያ 130 ሺህ ሰዎች አሁንም በባርነት ይኖራሉ ተባለ፡፡
ባርነት አልያም የባሪያ ንግድ ካቆመ አንድ ክፍለ ዘመን አልፎታል ቢባልም በብሪታንያ ግን አሁንም ዜጎች በባርነት እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡
ዓለም አቀፉ የጸረ ባርነት ተቋም ባወጣው ሪፖርት ከሆነ በብሪታንያ 130 ሺህ ዜጎች አሁንም ህይወታቸውን በዘመናዊ ባርነት ውስጥ እየመሩ ነው ብሏል፡፡
ይህን ተከትሎም የብሪታንያ መንግስት የፖሊሲ እና ህጋዊ እርምጃዎችን እንዲወስድ መጠየቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ዘመናዊ ባርነት ከሚባሉት ውስጥ ያለ ከፍያ ወይም በአነስተኛ ክፍያ የጉልበት ስራ ማሰራት፣ በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ውስጥ በግድ ማሳተፍ፣ የግዴታ ወሲብ ንግድ እና መሰል ስራዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በተጠናቀቀው የ2024 ዓመት ውስጥ ብቻ ከ17 ሺህ በላይ ጥቆማዎች ለሀገሪቱ መንግስት ደርሶታል ተብሏል፡፡
በዘመናዊ ባርነት ውስጥ ይኖራሉ ከተባሉ ዜጎች ውስጥ 30 በመቶዎቹ ብሪታንያዊያን ናቸው የተባለ ሲሆን አልባኒያ እና ቬትናማዊያንም አሉበት፡፡
በዚህ ዘመናዊ ባርነት ውስጥ ይኖራሉ ከተባሉት ውስጥ 31 በመቶ ያህሉ ደግሞ ህጻናት እንደሆኑም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
አብዛኞቹ በዚህ ጉዳት ውስጥ ያሉት ዜጎች ስደተኞች ናቸው የተባለ ሲሆን ወደመጡበት ሀገራት በጉልበት እንድንመለስ ልንደረግ እንችላለን የሚል ፍርሃት ያለባቸው ናቸውም ተብሏል፡፡