የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ክሃን “እኛ የምዕራባዊያን ባሪያዎች አይደለንም” አሉ
ጠ/ሚኒስትሩ ፓኪስታን ሩሲያን እንድታወግዝ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እናንተ ያላችሁትን ሁሉ ልንፈጽም አንችልም” ብለዋል
ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ብሪታኒያናን ጨምሮ 22 ሀገራት ፓኪስታን ሩሲያን እንድታወግዝ ጠየቁ
የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ክሃን “እኛ የምዕራባዊያን ባሪያዎች አይደለንም” አሉ።
ሩሲያ ጦሯን ለልዩ ተልዕኮ በሚል ወደ ዩክሬን ባስገባች በማግስቱ ወደ ሞስኮ አቅንተው የነበሩት የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ክሃን ሩሲያን እንዲያወግዙ ሲጠየቁ ቆይተዋል።
የ22 ሀገራት ትልልቅ ዲፕሎማቶች በጋራ በመሆን የፓኪስታን መንግስት ተመድ በሩሲያ ላይ ያዘጋጀውን የውሳኔ ሃሳብ እንዲደግፍ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ጥያቄውን በጋራ ካቀረቡት መካከል የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት እንደሚገኙበትም ተገልጿል። የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ሩሲያ “በዩክሬን ወረራ” እንደፈጸመች ተደርጎ የቀረበ ሲሆን፤ ኢስላማባድ ይህን እንድትደግፍ ጥያቄ ሲቀርብላት ቆይቷል።
የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት ሆነው ፓኪስታን ሩሲያን እንዲታወግዝ በፊርማ የጠየቁት ኦስትሪያ፣ ቤልጀም፣ ቡልጋሪያ፣ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ሃንጋሪ፣ ጣሊያን፣ ፖርቹጋል፣ ፖላንድ፣ ሮማኒያ፣ ስፔን፣ ስዊድን፣ እና ኔዘርላንድስ ናቸው።
ከዚህ ባለፈም አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድና ብሪታኒም ኢስላማባድ፣ ሞስኮን እንድታወግዝ በፊርማቸው የጠየቁ ናቸው።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሞስኮ ከመሄዳቸው አስቀድሞ የዩክሬን ቀውስ ከሀገራቸው ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር እንደሌለ የገለጹ ሲሆን፤ ኢስላማባድ የትኛውንም ወገን መቀላቀል እንደማትፈልግ በወቅቱ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት ምላሽ “እኛ ምዕራባዊያን ባሪያዎች አይደለንም ፣ ስለእኛ ምንድን ነው እምታስቡት፣ እናንተ ያላችሁትን ሁሉ ልንፈጽም አንችልም” ብለዋል።
ምዕራባዊያን ህንድ ወደ ፓኪስታን ካሽሚር ግዛት ገብታ በሀይል ስትቆጣጠር ምንም ትንፍሽ አላሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውሮፓዊያን ሚዛናዊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶ ጦሩን ወደ አፍጋኒስታን ሲያሰማራ ፓኪስታን ድጋፍ በመስጠቷ ብዙ ጉዳቶችን እንዳስተናገደችም ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን ተናግረዋል።
ፓኪስታን ከሩሲያ፣ ከአሜሪካ፣ ከቻይና እና አውሮፓ ጋር ወዳጅ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ክሃን እኛ የትኛውንም የሀይል አሰላለፍ መደገፍ እና መቃወም አንፈልግም ሲሉም አክለዋል።