ብሪታንያ በባሪያ ንግድ ወቅት ለፈጸመችው በደል 24 ትሪሊዮን ዶላር እንድትከፍል ተጠየቀ
የመንግስታቱ ድርጅት ዳኛ ብሪታንያ በ14 ሀገራት ላይ ለፈጸመችው በደል ካሳ መክፈል አለባት ብለዋል
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ግን ሀገራቸው ለፈጸመችው በደል ይቅርታም ሆነ ካሳ አትከፍልም ማለታቸው ተገልጿል
ብሪታንያ በባሪያ ንግድ ወቅት ለፈጸመችው በደል 24 ትሪሊዮን ዶላር እንድትከፍል ተጠየቀ።
በተመድ የፍትህ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ፓትሪክ ሮቢንሰን ብሪታንያ በካሪቢያን ሀገራት ላይ በፈጸመችው በደል 24 ትሪሊዮን ዶላር እንድትከፍል ጠይቀዋል።
ብሪታንያ በባሪያ ንግድ ወቅት በካሪቢያን ሀገራት ላይ ባደረሰችው በደል ምክንያት አያሌ ጉዳቶች ደርሰዋል ተብሏል።
ሀገሪቱ ላደረሰችው በደልም በካሳ መልክ ትክፈል የተባለው 24 ትሪሊዮን ዶላር ከደረሰው በደል አንጻር ትንሽ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
ዳኛ ሮቢንሰን " የተወሰኑ ሀገራት ስለ ዓለም ባርነት ሲነሳ ምንም እንዳልተፈጠረ አንገታቸውን ይደፋሉ፤ ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው፤ መንግስታቸው በአንድ ወቅት ለሰራው ስህተት ካሳ መክፈል ግዴታ አለባቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
በተመድ የፍትህ ፍርድ ቤት ስር ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ በትራንስ አትላንቲክ የተፈጸሙ የባሪያ ንግድ ጉዳት ጥናት ሪፖርት ይፋ መደረጉን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
በዚህ ሪፖርት መሰረት 31 ሀገራት በባሪያ ንግድ ላይ ተሳትፈዋል የተባለ ሲሆን እነዚህ ሀገራት ለተበዳይ ሀገራት 107 ትሪሊዮን ዶላር ካሳ መክፈል እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
የካሳ ክፍያው ስሌት የተሰራው የባሪያ ንግድ የፈጸሙ ሀገራት ያካበቱት ሀብት እና በሰዎች ላይ የተፈጸመው ጉዳትን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
የባሪያ ንግድ ካሳ ክፍያው በረጅም ጊዜ እንዲከፈል የተጠየቀ ሲሆን በወቅቱ የባሪያ ንግድ በደል አድርሰዋል የተባሉ ሀገራት ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ላይ ናቸው።
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሺ ሱናክ ብሪታንያ በባሪያ ንግድ ወቅት ለፈጸመችው በደል ይቅርታ እንድትጠይቅ እና ካሳ እንድትከፍል የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።
የሀገሪቱ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ከ16ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን በሚሊየን የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን በካርቢያን በእርሻ ስራ በሃይል እንዲሰማሩ ማድረጋቸውን መረጃዎች ያሳይሉ።
ብሪታንያ በ1833 በፓርላማ የባርያ ንግድን እንዲቆም ብታደርግም እስካሁን በመንግስት ደረጃ ይቅርታ አልጠየቀችም፤ ካሳ ለመክፈልም ፈቃደኛ አይደለችም።
ብሪታንያ፣ ስፔን፣ አሜሪካ እና ፈረንሳይ በጥቁር ሰዎች ላይ የባሪያ ንግድን በማካሄድ ብዙ በደሎችን የፈጸሙ እና የተትረፈረፈ ሀብት ያገኙ ሀገራት መሆናቸው ይነገራል።