ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ሩሲያ እና ዩክሬን የእስረኛ ልውውጥ ሲያደርጉ ይህ ለ56ኛ ጊዜ ነው
በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩሲያ እና ዩክሬን 206 የጦር እስረኞችን ተለዋውጠዋል።
ሀገራቱ አረብ ኤምሬትስ አደራዳሪነት በደረሱት ስምምነት ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዙሮች የእስረኛ ልውውጥ አድርገዋል።
በዚህኛው ዙር የእስረኞች ልውውጥ የተለቀቁት የዩክሬን ወታደሮች በምዕራብ ሩሲያ ኩርሰክ ግዛት ሲዋጋ የነበረው ጦር አባላት ናቸው ተብሏል፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሀይል ከእስር የተለቀቁትን ወታደሮቹን የስነልቦና እና አካዊ ህክምና ወደ ሚያገኙበት ተቋም መወሰዳቸውን አስታውቋል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዘለንስኪ 103 ጀግኖቻችንን አስለቅቀናል፤ ይህን የእሰረኞች ልውውጥ ላመቻቹ አካላት ምስጋናየን እገልጻለሁ ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
ዛሬ የተከናወነውን የእሰረኛ ልውውጥ በማደራደር በኩል ሚና የነበራት አረብ ኤሜሬትስ በአጠቃላይ 8 የተሳኩ የእስረኛ ልውውጦችን ማሸማገል ችላለች፡፡
አቡዳቢ ከዚህ የማሸማገል ስራዋ በተጨማሪ ጦርነቱ በድርድር እንዲቋጭ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ፍራንስ 24 አስነብቧል፡፡
ከሁለት አመት ተኩል ለተሻገረ ጊዜ በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ኪቭ እና ሞስኮ የተለያዩ የእስረኛ ልውውጥን ያደረጉ ሲሆን ይህኛው ለ56ኛ ጊዜ የተከናወነ ነው።
በተመሳሳይ ከሶስት ሳምንታት በፊት 115 እስረኞችን መለዋወጣቸው የሚታወስ ነው።
አረብ ኤሜሬትስ ፣ ቱርክ እና ሳኡዲ አረብያ የእሰረኛ ልውውጡ እንዲካሄድ ሀገራቱን በማደራደር ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሀገራት ናቸው፡፡
ሶስተኛ አመቱን ሊያስቆጥር የወራት እድሜ በቀሩት የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ሩሲያ እስካሁን የዩክሬንን 18 በመቶ ግዛት የተቆጣጠረች ሲሆን ዩክሬን በበኩሏ ባሳለፍነው ወር የሩሲያን ጦር ግስጋሴ ይቀለብሳል ያለችውን ጥቃት በኩርስክ ግዛት ዘልቆ በመግባት ድንገተኛ ጥቃት ፈጽማለች፡፡
ሞስኮ በበኩሏ ወሳኝ የሎጂስቲክ ማሳለጫ ነች የተባለችውን የፖክሮቨስክ ከተማን ለመቆጣጠር እያደረገች የምትገኘውን ውግያ አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
አሜሪካ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎች በሩሲያ ውስጥ ጥቃት ለመፈጸም እንዲውሉ ፈቃድ ለመስጠት እያጤነች መሆኗን ማስታወቋን ተከትሎ ሩሲያ ይህ ውሳኔ ጦርነቱ ቀጠናዊ መልክ እንዲይዝ የሚያደርግ ነው ስትል አስጠንቅቃለች፡፡