በዛምቢያ ከ400 በላይ ውሾችን የገደለው ምንድን ነው?
የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ሁኔታው ለሰው ልጆች ጤናም ስጋት ደቅኗል ብሏል
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በበቆሎ ምርት ላይ የተገኘው ኬሚካል ሰዎችን ለጉበት ካንሰር እንደሚያጋልጥ አስጠንቅቋል
በዛምቢያ ከ400 በላይ ውሾችን የገደለው ምንድን ነው?
በደቡብ አፍሪካዊቷ ዛምቢያ ከ400 በላይ ውሾች መሞታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ውሾቹ ከበቆሎ የተሰሩ ምግቦችን ከበሉ በኋላ ሞተዋል ተብሏል።
በዛምቢያ በቆሎ ዋና የምግብ አይነት ሲሆን የሀገሬው ዜጋ በተለያየ መልኩ በመስራት ይመገበዋል።
በመደብ ማዕድን ሀብታም የሆነችው ዛምቢያ የሀገሪቱ ምግብ 60 በመቶ ያህሉን ከበቆሎ እና ተያያዥ ምርቶች ያገኛል።
ከሰሞኑ ከበቆሎ ዱቄት የተሰሩ የታሸጉ ምግቦችን የተመገቡ ውሾች በድንገት እየሞቱ ነው ተብሏል።
ለውሾቹ መሞት ዋና ምክንያት ነው የተባለው ደግሞ በተለምዶ በምግቦች ላይ የሚፈጠረው ሻጋታ ነገር ወይም በሳይሳዊ ስሙ አፍላቶክሲን የተሰኘው ኬሚካል እንደሆነ ተገልጿል።
አፍላቶክሲን ተገኝቶባቸዋል የተባሉት የበቆሎ ምግቦች ከውሾች ባለፈ ሰዎችም አብዝተው የሚመገቧቸው መሆናቸውን ተከትሎ በዛምቢያ ፍርሀት ሰፍኗል።
ይህን ተከትሎም የሀገሪቱ ጤና ሚንስቴር ናሙናዎችን በመሰብሰብ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ላይ ሲሆን እስካሁን በአፍላቶክሲን ምክንያት የሞተ ሰው ስለመኖሩ እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ አፍላቶክስን የተሰኘው በምግቦች ላይ የሚገኘው ኬሚካል በምንመገባቸው ምግቦች ውስጥ መጠኑ ከፍ ካለ ለጉበት ካንሰር እንደሚያጋልጥ አስጠንቅቋል።
ሻጋታ ያለባቸው ምግቦችን አለመመገብ፣ አብስሎ መመገብ እና መልካቸውን እና ተፈጥሯዊ መዓዛቸውን የቀየሩ ምግቦችን አለመመገብ ደግሞ ራስን ከጉዳት መከላከያ መንገዶች ናቸው ተብላል።