ትራምፕ ረገብ ብሎ የነበረውን የንግድ ጦርነት አስጀመሩ
ከካናዳ እና ሜክሲኮ የሚገቡ ምርቶች ላይ የተጣለው የ25 በመቶ ታሪፍ ከዛሬ ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆን አዘዋል፤ በቻይና ደግሞ የ10 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ ጥለዋል

ሶስቱ የአሜሪካ ቀዳሚ የንግድ አጋሮች ለትራምፕ ታሪፍ አጻፋውን እንደሚመልሱ ዝተዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከካናዳ እና ሜክሲኮ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከዛሬ ጀምሮ የ25 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣል ገለጹ።
በየካቲት ወር መጀመሪያ የ10 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባት የነበረው ቻይና ደግሞ የ10 በመቶ ጭማሪ ተደርጎባት ምርቶቿ ወደ አሜሪካ ሲገቡ የ20 በመቶ ቀረጥ ይጣልባታል ብለዋል።
ትራምፕ ሶስቱ የአሜሪካ ቀዳሚ የንግድ አጋሮች ፌንታኒል የተሰኘውን ገዳይ አደንዛዥ እጽ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ መቆጣጠር አልቻሉም በሚል ነው ታሪፉን የጣሉት።
ቻይና በፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ለተጣለባት ታሪፍ ፈጣን ምላሽ ሰጥታለች፤ ከመጋቢት 10 2025 ጀምሮ በተወሰኑ ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ከ10 እስከ 15 በመቶ ታሪፍ እንደምትጥል አስታውቃለች።
ለሶስት አስርት አመታት ከአሜሪካ ጋር ከታሪፍ ነጻ የንግድ ትስስር የነበራቸው ካናዳ እና ሜክሲኮም በቀዳሚ የንግድ አጋራቸው ላይ የአጻፋ እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶው ኦታዋ 20.7 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ባላቸው የአሜሪካ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ እንደምትጥል ገልጸዋል።
በትራምፕ አስተዳደር ከዛሬ ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆን የታዘዘው ታሪፍ በ21 ቀናት ውስጥ ካልቆመም 86.2 ቢሊየን ዶላር በሚያወጡ የአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፍ እንደሚጣል ነው የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ቢራ፣ ወይን፣ ውስኪ፣ የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎች እና የፍሎሪዳ የብርቱካን ጭማቂ የታሪፉ ኢላማ እንደሚሆኑ መናገራቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
የኦንታሪዮ አስተዳዳሪ ዱንግ ፎርድ ግዛቷ ወደ አሜሪካ ኤሌክትሪክ ማስተላለፍና ንኬል መላክ እንደምታቆም ለኤንቢሲ ተናግረዋል።
የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሼንባም በአሜሪካ ላይ ስለሚወሰደው የአጻፋ እርምጃ የሚሰጡት መግለጫ እየተጠበቀ ነው።
በቻይና ላይ የተደራረበው ታሪፍ
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቤጂንግ ምርቶች ላይ የጣሉት የ20 በመቶ ታሪፍ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው 370 ቢሊየን ዶላር በሚያወጡ ወደ አሜሪካ በገቡ የቻይና ምርቶች ላይ ከጣሉት የ25 በመቶ ታሪፍ ላይ የሚደመር ነው።
በትራምፕ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን ታሪፍ የተጣለባቸው ምርቶች በባይደን አስተዳደርም ኢላማ ነበሩ። ባይደን ባለፈው አመት በቻይና "ሰሚኮንዳክተሮች" ላይ የ50 በመቶ፤ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ደግሞ የ100 በመቶ ታሪፍ መጣላቸው ይታወሳል።
ትራምፕ ዳግም ወደ ስልጣን ከተመለሱ በኋላ የጣሉት ታሪፍ ከዚህ በፊት በነበሩት ውሳኔዎች ያልተካተቱን እንደ ስማርት ስልኮች፣ ላፕቶፖች፣ ስማርት ስአቶች እና ድምጽ ማጉያዎች ቀረጥ እንዲጣልባቸው የሚያደርግ ነው።
ቤጂንግ በዛሬው እለት ይፋ ባደረገችው የአጻፋ ምላሽ ከአሜሪካ የሚገቡ እንደ ስጋ፣ የግብርና ምርቶች፣ ፍራፍሬ እና አትክልቶች እንዲሁም የወተት ውጤቶች ተጨማሪ ከ10-15 በመቶ ታሪፍ ይጣልባቸዋል።
የሀገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር ዋሽንግተን የገጠማትን የፌንታኒል ቀውስ "በቻይና ላይ ለማላከክ" እየሞከረች ነው ሲል ወቀሳውን ማጣጣሉን ግሎባል ታይምስ አስነብቧል።