ፓኪስታን በታጣቂዎች ታግቶ ከነበረው ባቡር ከ300 በላይ ሰዎችን ማስለቀቋን ገለጸች
ለ30 ስአታት በተካሄደው ታጋቾቹን የማስለቀቅ ልዩ ዘመቻ 33 ታጣቂዎች መገደላቸውንም አስታውቃለች

440 የሚጠጉ ሰዎችን ያሳፈረውን ባቡር ያገቱት የባሎቺ ነጻ አውጪ ቡድን ታጣቂዎች ናቸው
የፓኪስታን ጦር በባቡር ሲጓዙ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ ከ300 በላይ ሰዎችን ማስለቀቁን ገለጸ።
ጦሩ በባሎቺስታን ግዛት በታጣቂዎች የታገተው የመንገደኞች ባቡር ውስጥ የነበሩ ሰዎችን ለማስለቀቅ 30 ስአታት የፈጀ ልዩ ዘመቻ አካሂዷል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እና ሄሊኮፕተሮች በተሳተፉበት ዘመቻ 33 የባሎቺ ነጻ አውጪ ግንባር ታጣቂዎች መገደላቸውን ነው የፓኪስታን ጦር ቃል አቀባይ የተናገሩት።
ታጣቂዎቹ ባቡሩን እንዳገቱ በከፈቱት ተኩስ 21 ንጹሃን መንገደኞች እና አራት ወታደሮች መገደላቸውም ተገልጿል።
440 የሚጠጉ ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ ከነበረው ባቡር ውስጥ በፓኪስታን ጦር ልዩ ዘመቻ ከ300 በላዩ ነጻ መውጣታቸው የተነገረ ሲሆን፥ ተኩስ ሲከፈት እግሬ አውጪኝ ብለው የሮጡ መንገደኞችን የማፈላለግ ጥረቱ ቀጥሏል።
ከጥቃቱ ሸሽተው ካመለጡት መንገደኞች ውስጥ ለአራት ስአታት በጨለማ ተጉዞ በቀጣዩ የባቡር ጣቢያ የደረሰው ሙሃመድ አሽራፍ አንዱ ነው።
ሙሃመድ ከኩይታ ወደ ላሆር ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ሲጓዝ ያጋጠመውን ክስተት "የምጽአት ቀን" የመሰለ አስፈሪ ነገር ነበር ይላል። "ህጻናት እና ሴቶች ጋር ስለነበርን ከስአታት አድካሚ ጉዞ በኋላ በቀጣዩ የባቡር ጣቢያ የደረስነው እጅግ በጣም ዝለን ነው" ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።
የባቡር እገታው የተፈጸመበት አካባቢ ስልክም ሆነ ኢንተርኔት የሌለበት መሆኑም የጸጥታ አካላት በፍጥነት እንዳይደርሱላቸው ማድረጉ ነው የተገለጸው።
ታጣቂዎቹ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ መንገደኞችን አግተው መውሰዳቸውንና የባሎቺ የፖለቲከኛ እስረኞች በ48 ስአት ውስጥ ካልተለቀቁ ታጋቾቹን እንደሚገድሉ ማስጠንቀቃቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ፓኪስታን፣ አሜሪካ እና ብሪታንያን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን ሀገራት የባሎቺስታን ግዛትን ነጻ ሀገር የማድረግ ውጥን ያለውን የባሎች ነጻ አውጪ ግንባር በሽብርተኛ ቡድንነት ፈርጀውታል።
ኢስላማባድ የባሎቺስታን ግዛትን ውድ የማዕድን ሃብት ያለአግባብ እየበዘበዘች ነው ሲል የሚከሰው ቡድኑ በሀገሪቱ ወታደራዊ ካምፖች፣ የባቡር ጣቢያዎች እና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ፈጽሟል።